በከተማዋ በዓሉን ምክንያት በማድረግ የዋጋ ጭማሪ ባደረጉ እና ምርቶችን በደበቁ የንግድ ተቋማት ላይ ህጋዊ እርምጃ ተወሰደ - ኢዜአ አማርኛ
በከተማዋ በዓሉን ምክንያት በማድረግ የዋጋ ጭማሪ ባደረጉ እና ምርቶችን በደበቁ የንግድ ተቋማት ላይ ህጋዊ እርምጃ ተወሰደ
ጅማ ፤ሚያዝያ 3/2018 (አዜአ)፡-በጅማ ከተማ በዓሉን ምክንያት በማድረግ የዋጋ ጭማሪ ባደረጉ እና ምርቶችን በደበቁ የንግድ ተቋማት ላይ ህጋዊ እርምጃ መወሰዱን የከተማዋ ንግድ ፅህፈት ቤት አስታውቋል።
የጅማ ከተማ ንግድ ፅህፈት ቤት ኃላፊ ወይዘሮ ረውዳ ጀማል ለ ኢዜአ እንዳሉት፤ በዓሉን ምክንያት በማድረግ የተጋነነ እና ያልተገባ የዋጋ ጭማሪ ባደረጉ እና ምርትን በደበቁ 24 የንግድ ተቋማት ላይ ህጋዊ እርምጃ ተወስዷል።
የፋሲካ በዓልን እና አንዳንድ ወቅታዊ ሁኔታን ተገን በማድረግ በሸቀጦች ላይ የዋጋ ጭማሪ በሚያደርጉ የንግድ ተቋማት ላይ የሚወሰደው ህጋዊ እርምጃ ተጠናክሮ ቀጥሏል ብለዋል።
የንግድ ተቋማቱ በከተማው ውስጥ በቂ ምርቶች እያሉ ምርትን በመደበቅ፣ በሸቀጦች ላይ ያልተገባ የዋጋ ጭማሪ በማድረግ እና ያለ ደረሰኝ በመሸጥ ህብረተሰቡን ለእንግልት የመዳረግ ህገወጥ ተግባር መፈጸማቸውን ጠቅሰዋል።
በዚህም 25 የንግድ ተቋማት እንዲታሸጉ እና ፍቃዳቸው እንዲነጠቅ ሲደረግ፣ ለ 17 የንግድ ተቋማት ደሞ ማስጠንቀቂያ መሰጠቱን አብራርተዋል።
በከተማዋ በቂ ምርቶች እና የበዓል ግብዓቶች እየቀረቡ ነው ያሉት ኃላፊዋ ህብረተሰቡ የግብዓት እጥረት ያለ በማስመሰል የዋጋ ጭማሪ የሚያደርጉ አካላትን ሲመለከት ጥቆማ እንዲሰጥም ጠይቀዋል።
የአለም አቀፍ ሁኔታዎችንም ሆነ የህዝብ በዓላትን ምክንያት በማድረግ የተጋነነ የሸቀጦች ዋጋ ጭማሪ የሚያደርጉ ህገወጥ ነጋዴዎች ላይ እየተወሰደ ያለው እርምጃ ተጠናክሮ እንደሚቀጥልም አረጋግጠዋል።
የንግዱ ማህበረሰብ አባላት ማህበረሰቡን በታማኝነት ሊያገለግሉት እንደሚገባ ኃላፊዋ አመልክተው ሸማቾችም መሰል ህገወጥ ተግባራትን ሲመለከቱ ለሚመለከተው የህግ አካል ጥቆማ እንዲሰጡም አሳስበዋል።