የትንሳዔ በዓልን ስናከብር በታላቅ ፍቅር እና መተሳሰብ ሊሆን ይገባል - ከንቲባ አዳነች አቤቤ - ኢዜአ አማርኛ
የትንሳዔ በዓልን ስናከብር በታላቅ ፍቅር እና መተሳሰብ ሊሆን ይገባል - ከንቲባ አዳነች አቤቤ
አዲስ አበባ፤ ሚያዚያ 3/2018 (ኢዜአ)፦ የትንሳዔን ምሳሌነት መሰረት በማድረግ በታላቅ ፍቅር እና መተሳሰብ በዓሉን ማክበር እንደሚገባ የአዲስ አበባ ከተማ ከንቲባ አዳነች አቤቤ ገለጹ፡፡
ከንቲባ አዳነች አቤቤ ዛሬ በትንሣኤ በዓል ዋዜማ በጎ ፈቃደኞችን በማስተባበር የተገነቡ 215 ዘመናዊ የመኖሪያ ቤቶች ከተለያዩ ክፍለ ከተሞች ለተውጣጡ አቅመ ደካሞች፣ አካል ጉዳተኞች፣ ለአገር ባለውለታዎችና ለልማት ተነሺዎች ከሙሉ የቤት ቁሳቁስና ከበዓል መዋያ ጋር በስጦታ አበርክተዋል፡፡
የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ከንቲባ አዳነች አቤቤ በዚሁ ወቅት፤ የከተማ አስተዳደሩ ከህዝብ ጋር በመሆን በርካታ የልማት ሥራዎችን እያከናወነ እንደሚገኝ ገልጸዋል።
መንግስት በጎ ፈቃደኞችን በማስተባበር ያስገነባቸውን 215 ቤቶች መገንባቱን አመልክተው፤ መኖሪያ ቤቶች በተለያዩ ክፍለ ከተሞች ይኖሩ ለነበሩ አቅመ ደካሞች፣ አካል ጉዳተኞች፣ ሀገር ባለውለታዎችና ልማት ተነሺዎች ከሙሉ የቤት ቁሳቁስና ከበዓል መዋያ ጋር በስጦታ አበርክተናል ብለዋል።
የበጎነት የመኖሪያ መንደር ቀደም ሲል የአንድ አባወራ ይዞታ ብቻ እንደነበር አስታውሰው፤ አሁን ላይ ለ40 አባወራዎች የሚሆን ዘመናዊ መኖሪያ ቤት ተገንብቶበታል ነው ያሉት።
ይህ የግንባታ ሂደትም ትንሽ ቦታን በአግባቡ አልቆ በጋራ የመጠቀም እሳቤን በተግባር ያሳየ መሆኑን አስገንዝበዋል።
የኦሮሚያ ባንክ ከ80 ሚሊዮን ብር በላይ ወጪ በማድረግ 40 አባወራዎችን መያዝ የሚችል ባለ አራት ወለል ህንፃ በማስገንባት ማህበራዊ ኃላፊነቱን መወጣቱን ተናግረዋል።
ስንተባበር ከተማችን ይዘምናል፤ ኑሮአችንም ክብራችንን የጠበቀ ይሆናል ያሉት ከንቲባ አዳነች፤ ኑሮ እና ሁለንተናዊ ዕድገት እንደሚመጣ ገልጸዋል።
በሁሉም ክፍለ ከተሞች ማህበራዊ ኃላፊነታቸውን በመወጣት የመኖሪያ መንደሮችን ለዜጎች የገነቡ አካላትን አመስግነው፤ ለመላው የክርስትና እምነት ተከታዮች ለትንሳዔ በዓል የእንኳን አደረሳችሁ መልዕክት አስተላልፈዋል።
የኦሮሚያ ባንክ ቦርድ ሰብሳቢ አሰፋ ስሜ (ዶ/ር) በበኩላቸው፤ መንግስት በማከናወን ላይ ያለው አካታች እና ሰው ተኮር ልማት የሚደነቅ ነው ብለዋል።
ባንኩ ከመንግስት ጋር በመተባበር ለዜጎች መኖሪያ በመገንባቱም የተሰማቸውን ደስታ ገልጸው፤ ይህን ተግባር በቀጣይም አጠናክሮ እንደሚቀጥል አስረድተዋል።