ህዝበ ክርስቲያኑ በዓሉን ሲያከብር የተቸገሩትን በመርዳትና ጥልን በይቅርታ በመሻገር ሊሆን ይገባል--የሃይማኖት አባቶች - ኢዜአ አማርኛ
ህዝበ ክርስቲያኑ በዓሉን ሲያከብር የተቸገሩትን በመርዳትና ጥልን በይቅርታ በመሻገር ሊሆን ይገባል--የሃይማኖት አባቶች
ዲላ፤ ሚያዝያ 3/2018 (ኢዜአ) ፡-ህዝበ ክርስቲያኑ የትንሣኤን በዓልን ሲያከብር የተቸገሩትን በመርዳት፣ ከክፉ ሥራ በመራቅና ጥልን በይቅርታ በመሻገር ሊሆን እንደሚገባ በዲላ ከተማ አስተያየታቸውን ለኢዜአ የሰጡ የሃይማኖት አባቶች ገለጹ።
የትንሣኤ በዓል ኢየሱስ ክርስቶስ ለሰው ልጆች መዳን መከራን በመቀበል ሞትን ድል አድርጎ የተነሳበት በመሆኑ ልዩ ትርጉም ተሰጥቶ የሚከበር መሆኑን ነው የሃይማኖት አባቶቹ ያነሱት።
በመሆኑም ምዕመኑ በዓሉን ሲያከብር ልዩነቶችን በማጥበብ፣ ከክፉ ሥራ በመራቅ፣ ጥልን በይቅርታ በመሻገር፣ ለሀገር ሰላምና አንድነት በጋራ በመቆም ሊሆን እንደሚገባም መልዕክት አስተላልፈዋል።
ለኢዜአ አስተያየታቸውን የሰጡ የዲላ ደብረ ገነት ቅዱስ ሚካኤል ቤተክርስቲያን ስብከተ ወንጌል ሃላፊ መጋቤ ሀዲስ ኤልያስ ብዙነህ የትንሣኤ በዓል ኢየሱስ ክርስቶስ ለሰው ልጆች መዳን መከራን በመቀበል ሞትን ድል አድርጎ የተነሳበት መታሰቢያ እለት ነው።
ከትንሳኤ የተማርነው ፍቅርንና ይቅርታን በመተግበር፣ የተቸገሩትን በመርዳትና በመተጋገዝ በዓሉን ማሳለፍ ነው ሲሉም አመልክተዋል።
ትንሣኤ የፍቅርና የምህረት በዓል መሆኑን የገለፁት ደግሞ በኢትዮጵያ ካቶሊክ ቤተክርስቲያን የዲላ ክርስቲያኖች ረዳት ማርያም ቁምስና ቆሞስ አባ ፍስሃየ መለስ ናቸው።
ምዕመኑ በዓሉን ሲያከብር ልዩነቶችን በማጥበብ፣ ከክፉ ሥራ በመራቅ፣ ጥልን በይቅርታ በመሻገርና ለሀገር ሰላምና አንድነት በጋራ በመቆም ሊሆን እንደሚገባም ገልፀዋል።
በተለይም በበዓሉ ወቅት አቅመ ደካሞችንና ረዳት የሌላቸውን ወገኖች በማሰብና ካለን ላይ በማካፈል በዓሉን በበረከት ማክበር እንደሚገባ አሳስበዋል።
የዲላ የካህናት መቅደስ ቤተክርስቲያን መጋቢ ሕርባዬ ደበበ በበኩላቸው ትንሳኤ ኢየሱስ ክርስቶስ ሞትን ድል አደርጎ በመነሳት የሰው ልጆችን የሃጥያት እዳ የከፈለበት በመሆኑ ልዩ ትርጉም ያለውና በድምቀት የሚከበር በዓል ነው ብለዋል።
ትንሳኤ አምላክ ሰው በመሆን ለሰው ልጆች ያለውን ፍቅርና ርህራሄ እንዲሁም ምህረትን ያስተማረበት መሆኑን አንስተው እኛም ከዚህ በመማር በዓሉን ስናከብር በይቅርታና በሰላም መሆን አለበት ብለዋል።