ከንቲባ አዳነች አቤቤ ለአቅመ ደካሞች፣ ለአካል ጉዳተኞች፣ ለአገር ባለውለታዎችና ለልማት ተነሺዎች የመኖሪያ ቤቶችን አበረከቱ - ኢዜአ አማርኛ
ከንቲባ አዳነች አቤቤ ለአቅመ ደካሞች፣ ለአካል ጉዳተኞች፣ ለአገር ባለውለታዎችና ለልማት ተነሺዎች የመኖሪያ ቤቶችን አበረከቱ
አዲስ አበባ፤ ሚያዚያ 3/2018 (ኢዜአ)፦ የአዲስ አበባ ከተማ ከንቲባ አዳነች አቤቤ በተለያዩ ክፍለ ከተሞች ለሚገኙ አቅመ ደካሞች፣ አካል ጉዳተኞች፣ ለአገር ባለውለታዎችና ለልማት ተነሺዎች የመኖሪያ ቤቶችን ከሙሉ የቤት ቁሳቁስና ከበዓል መዋያ ጋር በስጦታ አበረከቱ።
ከንቲባዋ በማህበራዊ ትስስር ገፃቸው ባስተላለፉት መልእክት ሁልጊዜም በበዓላት ወቅት እንደምናደርገው፣ ዛሬ በትንሣኤ በዓል ዋዜማ በከተማችን የተለያዩ አካባቢዎች በጎ ፈቃደኞችን በማስተባበር የገነባናቸውን 215 ዘመናዊ የመኖሪያ ቤቶች፤ በተለያዩ ክፍለ ከተሞች ለሚገኙ ለአቅመ ደካሞች፣ ለአካል ጉዳተኞች፣ ለአገር ባለውለታዎችና ለልማት ተነሺዎች ከሙሉ የቤት ቁሳቁስና ከበዓል መዋያ ጋር በስጦታ አበርክተናል ብለዋል።
በከተማችን የበጎ ፈቃድ ተግባር ከጊዜ ወደ ጊዜ እየጎለበተና ባህል እየሆነ መምጣቱ የሚያስደስት ነው። ይህንን በጎ ተግባር በተለያየ መልኩ ለደገፋችሁ ልበ ቀና በጎ ፈቃደኞች፣ ተቋማትና አመራሮች በሙሉ በተለይም ከ 80 ሚሊዮን ብር በላይ ድጋፍ ላደረገው የኦሮሚያ ባንክ በተጠቃሚዎች ስም ከልብ የመነጨ ምስጋናዬን አቀርባለሁ ሲሉ ገልፀዋል።
የትንሣኤ በዓል ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ለሰው ልጆች ሁሉ በፍቅር ራሱን እስከ መስቀል የሰጠበት እና በትንሣኤ የምሥራች የተበሰረበት ነው። በመሆኑም በዓሉን ስናከብር ትንሳኤን ዓላማ እና ምሳሌነት መሰረት በታላቅ ፍቅር እና መተሳሰብ ሊሆን ይገባል ።
ድጋፍ ለሚሹ ወገኖቻችን ያለንን መተሳሰብ በተግባር የምንገልጽበት፣ አንዳችን ለሌላችን የደስታ፣ የሰላም እና የአብሮነት ምክንያት የምንሆንበት በዓል እንዲሆን ተመኝተዋል።