ቀጥታ፡

ለትንሳኤ በዓል በቂ ምርት ወደ ገበያ በመቅረቡ በተረጋጋ ሁኔታ እየተገበያየን ነው - የሚዛን አማን ከተማ ነዋሪዎች

ሚዛን አማን፣ ሚያዝያ 3/2018 (ኢዜአ) ፡-ለትንሳኤ በዓል በቂ ምርት ወደ ገበያ በመቅረቡ ተረጋግተው እየተገበያዩ መሆኑን የሚዛን አማን ከተማ ነዋሪዎች ተናገሩ።

ነዋሪዎቹ አቅማቸው በፈቀደው መልኩ በመሸመት በዓሉን ከጎረቤቶቻቸው ጋር በደስታ ለማክበር መዘጋጀታቸውንም ገልጸዋል።

አስተያየታቸውን ለኢዜአ የሰጡ የሚዛን አማን ከተማ ነዋሪዎች ለትንሳኤ በዓል በቂ ምርት ወደ ገበያ በመቅረቡ በተረጋጋ ሁኔታ እየተገበያዩ መሆኑን ገልጸዋል፡፡


 

ከአስተያየት ሰጪዎቹ መካከል ወይዘሮ ጨነቁ በፍቃዱ በምርቶች ላይ የተወሰነ የዋጋ ጭማሪ ቢኖርም ሁሉንም ምርቶች በተለያየ ዋጋና መጠን አማራጭ እያገኘን ነው ብለዋል። 

ከነዳጅ እጥረት ጋር ተያይዞ በተለይ የፋብሪካ ውጤቶችና ከሌላ አካባቢ የሚጫኑ የፍጆታ ምርቶች እጥረት ይከሰታል የሚል ስጋት እንደነበረባቸው ገልጸው ለምርት አቅርቦት መንግሥት በሰጠው ትኩረት ምንም እጥረት አለመከሰቱን ተናግረዋል።

በመንግሥት የሚደረገው የዋጋ ቁጥጥርና የምርት ክትትል በሌሎችም ጊዜያት ተጠናክሮ ሊቀጥል እንደሚገባም አመልክተዋል።


 

ወይዘሮ ባንቻለም አሉላ የተባሉ ሌላዋ የሚዛን አማን ከተማ ነዋሪ በበኩላቸው የተሻለ የበዓል ዋዜማ ድባብ ገበያ ላይ መኖሩን ገልጸዋል።

ቀይና ነጭ ሽንኩርት በተመጣጣኝ ዋጋ መሸመታቸውን ገልጸው በተለይ የሰንበት ገበያ ላይ ምርት በስፋት መቅረቡ የግብይት አማራጩን እንዳሰፋ ነው የተናገሩት።

የእርድ እንስሳት ዋጋ ጭማሪ ቢኖርም አቅማቸው የሚፈቅደውን መርጠው እየሸመቱ መሆኑን የተናገሩት ደግሞ መምህር አየለ ደሳለኝ የተባሉ የከተማዋ ነዋሪ ናቸው።


 

የእርድ እንስሳት መጠነኛ ጭማሪ ማሳየታቸውን ገልጸው በገበያው ግን በግ እና ዶሮ እንደልብ በመቅረባቸው በአማራጭ እየተገበያዩ መሆኑን ገልጸዋል።

የቤንች ሸኮ ዞን ንግድ እና ኢንቨስትመንት መምሪያ የሸማች ዘርፍ ባለሙያ አቶ አፈራ አያሌው ለዘንድሮ የፋሲካ በዓል ጠንካራ የገበያ ትስስር በመፍጠር ምርት ለገበያ እንዲቀርብ መደረጉን ገልጸዋል።


 

የፋብሪካ ውጤቶችን ከጅምላ ነጋዴዎች ጋር በመነጋገር በሰንበት ገበያ ላይ በተመጣጣኝ ዋጋ እንዲያገበያዩ ማድረግ መቻሉን አመልክተዋል።

ሕገ ወጥነትን ለመከላከል እየተደረገ ባለው ጠንካራ ክትትል ያለ አግባብ በሚንቀሳቀሱ ነጋዴዎች ላይ እርምጃ በመውሰድ የበዓል ገበያውን የተረጋጋ ማድረግ መቻሉን ጠቁመዋል።

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም