ሕዝበ ክርስቲያኑ የትንሳኤ በዓልን በአብሮነት እና በመረዳዳት ሊያሳልፍ ይገባል - የኃይማኖት አባቶች - ኢዜአ አማርኛ
ሕዝበ ክርስቲያኑ የትንሳኤ በዓልን በአብሮነት እና በመረዳዳት ሊያሳልፍ ይገባል - የኃይማኖት አባቶች
አዲስ አበባ ሚያዝያ 3/2018 (ኢዜአ)፦ ሕዝበ ክርስቲያኑ የትንሳኤን በዓል የአንድነትና የቸርነት እሴቶችን በማጎልበት፣ በመረዳዳትና በአብሮነት እንዲያሳፍል የኃይማኖት አባቶች ጥሪያቸውን አስተላልፈዋል።
የኃይማኖት አባቶቹ በመልዕክታቸው፤ በዓሉ ኢትዮጵያዊ አብሮነትንና የቸርነት እሴትን በማጠናከርና የተቸገሩ ወገኖችን በመርዳት ማክበር ይገባል ብለዋል።
ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ማትያስ ቀዳማዊ ፓትርያርክ ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ዘ ኢትዮጵያ ሊቀ ጳጳስ ዘ አክሱም ወእጨጌ ዘመንበረ ተክለሃይማኖት ባስተላለፉት መልእክት፤ የትንሳኤ በዓልን ሃይማኖቱ የሚያስተምራቸውን መልካም ስራዎች በተግባር በመግለጽ ልናከበር ይገባል ብለዋል፡፡
የበዓሉ መገለጫ ዕሴት የሆነውን መልካም ስብዕና እና ቅን አስተሳሰብ መጠቀም አስፈላጊ መሆኑን አመልክተው፤ በዓለም አቀፍ ደረጃም ሆነ በሀገርም የሚያጋጥሙ ፈተናዎችን በጽናት ማለፍ እንደሚገባ ተናግረዋል።
ምዕመናን በዓሉን ሲያከብሩ የተቸገሩ ወገኖችን በማሰብ እና በማገዝ አስፈላጊ መሆኑን ገልጸዋል።
የኢትዮጵያ ካቶሊካዊት ቤተ ክርስቲያን ሊቀ ጳጳሳት ብፁዕ ካርዲናል አቡነ ብርሃነ ኢየሱስ በበኩላቸው፤ ምዕመናን ከፈጣሪያቸው የተማሩትን በጎ ምግባር በተግባር እንዲያሳዩ ጥሪ አቅርበዋል።
ሕዝበ ክርስቲያኑ ከቂም በቀልና ከጥላቻ በመራቅ፣ ከሌሎች ወንድምና እህቶቻቸው ጋር በመተባበር ለሀገር ሰላምና ፍቅር መስራት እንዳለባቸው ገልጸዋል።
በተለያዩ አካባቢዎች በችግር ውስጥ የሚገኙ ዜጎችን መርዳትና መደገፍ የበዓሉ ዋነኛ መገለጫ ሊሆን እንደሚገባም አክለው ገልጸዋል።
የኢትዮጵያ የወንጌል አማኞች አብያተ ክርስቲያናት ካውንስል ፕሬዚዳንት ቄስ ደረጀ ጀንበሩ፣ ትንሳኤ ፈጣሪ ለሰው ልጆች ያለውን ጥልቅ ፍቅር የገለጸበት በዓል መሆኑን ገልጸዋል።
ትንሳኤ ጥላቻ በፍቅር፣ መለያየት በአንድነት፣ እንዲሁም ሽንፈት በድል የተተካበት መሆኑን አመልክተው፤ በምዕመናን ዘንድ ይቅር ባይነት ሊነግስ እንደሚገባ ተናግረዋል።
ኢትዮጵያ ልጆቿ ሰርተው የሚለወጡባት ምቹ ሀገር እንድትሆን ሁላችንም እርስ በእርስ ልንደጋገፍ ይገባል ሲሉ መልዕክታቸውን አስተላልፈዋል።
የሃይማኖት አባቶቹ በመልዕክታቸው ማጠቃለያ ላይ በዓሉ የሰላም፣ የፍቅርና የደስታ እንዲሆን ለሁሉም የክርስትና እምነት ተከታዮች መልካም ምኞታቸውን ገልጸዋል።