ቀጥታ፡

በዓሉን በአብሮነት እና በመተሳሰብ ለማሳለፍ ተዘጋጅተናል -የጅማ ከተማ የክርስትና እምነት ተከታዮች

ጅማ፤ ሚያዚያ 3/2018(ኢዜአ)፡- የትንሳኤ በዓልን በአብሮነት እና በመተሳሰብ ለማሳለፍ መዘጋጀታቸውን የጅማ ከተማ የክርስትና እምነት ተከታዮች ተናገሩ።

የጅማ ከተማ ነዋሪው አንዱአለም አለማየሁ፣ በተለይም ባለፉት 7 ዓመታት አቅመ ደካሞችን በማገዝ፣ በመመገብ እና በመንከባከብ እያሳለፈ መሆኑን ይናገራል። 

"አልባሳትን ለሌላቸው በመስጠት፣ ከምንመገበው በማካፈል ለወገኖቻችን አለን ልንል ይገባል" የሚለው ወጣቱ፤ ሰዎች ካላቸው በማካፈል ለራሳቸው ብቻ ሳይሆን ለሌሎችም ደስታ መትረፍ አለባቸው ሲል መልዕክቱን ያስተላልፋል።

ሌላኛዋ ነዋሪ ሃና ፀጋዬ የፋሲካ በዓልን በየዓመቱ ወደ በጎ አድራጎት ተቋማት በመሄድ እንደምታሳልፍ ትናገራለች። 

"በዓሉ ሙሉ የሚሆነው የተቸገሩትን ስናስብ እና ከጎናቸው ስንቆም ነው" የምትለው ሃና፤ ዘንድሮም  በከተማዋ ወደሚገኙት "የሰው ለሰው" እና "መቄዶንያ" በጎ አድራጎት ተቋማት በመሄድ በዓሉን ለማሳለፍ ዝግጅት ማድረጓን ተናግራለች።

ሌላኛው ነዋሪ መኮንን ገብሩ በአካባቢያችን እና በጎረቤት ብዙ ሊታገዙ የሚገቡ ሰዎችን በማሰብ ከልጆቻቸው ጋር በደስታ እንዲያሳልፉ ልናግዝ ይገባል ብሏል።

"በዓልን ያለ አብሮነት እና መተሳሰብ ማክበር ትርጉም አይሰጠኝም" የሚለው ደግሞ የጅማ ከተማ ነዋሪው ይሁኔ ጌታቸው ነው። 


 

በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስትያን  የጅማ የም እና ሰሜን ጎንደር ሀገረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ ብፁዕ አቡነ እስጢፋኖስ በበኩላቸው ''ክርስቶስ የተወልንን ምሳሌ በመከተል ለአቅመ ደካሞች ከማዘን ባለፈ በተግባር ከጎናቸው ቆመን ልናግዛቸው ይገባል'' ብለዋል።

የትንሳኤ በዓል በዕምነቱ ተከታዩች ዘንድ ክርስቶስ ከሞት መነሳቱ የሚታሰብበት ትልቅ በዓል መሆኑን አስታውሰው ይህን በዓል ክርስቶስ የተወልንን ምሳሌ በመከተል አቅመ ደካሞችን በተግባር በማገዝ ማሳለፍ ያስፈልጋል ሲሉ ገልፀው እኛም ካለን በማካፈል ምሳሌዉን ልንከተል ይገባል ብለዋል።

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም