ቀጥታ፡

ለትንሳኤ በዓል የሚሆኑ የፍጆታ ምርቶችን በተመጣጣኝ ዋጋ እና በበቂ ሁኔታ እያገኘን ነው

አዲስ አበባ፤ ሚያዚያ 3/2018 (ኢዜአ)፦ ለትንሳኤ በዓል የሚሆኑ የፍጆታ ምርቶችን በተመጣጣኝ ዋጋ እና በበቂ ሁኔታ እያገኙ መሆኑን ኢዜአ ያነጋገራቸው ሸማቾች ተናገሩ፡፡

በመዲናዋ የትንሳኤ በዓልን ምክንያት በማድረግ የተዘጋጁ የንግድ ባዛሮች የግብርና እና የኢንዱስትሪ ምርቶች ለሸማቾች ሰፊ አማራጭ ይዘው ቀርበዋል።

በተለይም እንደ እንቁላል፣ ቅቤ፣ ሽንኩርትና የቅመማ ቅመም ዓይነቶች እንዲሁም የባህል አልባሳት በከፍተኛ መጠን እየቀረቡ ይገኛል።

የምርት አቅርቦቱን አስመልክቶ ኢዜአ ያነጋገራቸው ነዋሪዎች እንደገለጹት፤ አስፈላጊ የበዓል ግብዓት በበቂ ሁኔታ ማግኘት ችለዋል። ከበዓሉ ጋር ተያይዞ ካለው ፍላጎት አኳያም የዋጋው ሁኔታ ተመጣጣኝ ነው።

ከሸማቾች መካከል አስተያየታቸውን የሰጡት አቶ እሸቱ ተሾመ እንዳሉት፤ በመዲናዋ በተዘጋጁ የተለያዩ ባዛሮች ላይ ለበዓል የሚያስፈልጉ ምርቶችን በተመጣጣኝ ዋጋ አግኝተዋል።

ሌላኛው ሸማች አቶ ጸጋዬ ደምሴ በበኩላቸው፤ በተዘጋጀው ኤግዚብሽንና ባዛር የሚፈልጓቸውን ዕቃዎች በአንድ ቦታና በተመጣጣኝ ዋጋ መግዛት መቻላቸውን ተናግረዋል።

ለበዓሉ አስፈላጊ የሆኑ ምርቶችን ከአምራቾች በቀጥታ ማግኘት ችያለሁ ያሉት ደግሞ አቶ አብርሃም ቦጋለ ናቸው።

በባዛሩ ላይ የባህል አልባሳትን ያቀረቡት ነጋዴ ትርሲት አበበ በበኩላቸው  በመደበኛ ሱቆች ከሚሸጡበት ዋጋ በቅናሽ ማቅረባቸውን በመግለጽ፤ ህብረተሰቡም የቀረበውን የዋጋ አማራጭ በመጠቀም እየገዛ እንደሚገኝ ተናግረዋል።

በተመሳሳይ መልኩ የማር ምርት ይዘው የቀረቡት አቶ አብርሃም ሞላ፤ በተመጣጣኝ ዋጋ ለገበያ ማቅረባቸውንና ሸማቹም በአቅርቦቱ ረክቶ ግብይት እያከናወነ መሆኑን ገልጸዋል።

የቆዳ ውጤቶችን ለገበያ ያቀረበችው ነጋዴ ፋይዛ ኸይሩ እንደተናገረችው፤ ሸማቹ ለበዓል ስጦታ የሚሆኑ ዕቃዎችን እየገዛ ይገኛል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም