ዌስትሃም ዩናይትድ ከወራጅ ቀጠና የወጣበት ወሳኝ ድል ተቀዳጅቷል - ኢዜአ አማርኛ
ዌስትሃም ዩናይትድ ከወራጅ ቀጠና የወጣበት ወሳኝ ድል ተቀዳጅቷል
አዲስ አበባ፤ ሚያዝያ 3/2018 (ኢዜአ)፦ በእንግሊዝ ፕሪሚየር ሊግ የ32ኛ ሳምንት የመጀመሪያ መርሐ ግብር ዌስትሃም ዩናይትድ ዎልቭስን 4 ለ 0 በሆነ ሰፊ የግብ ልዩነት አሸንፏል።
ትናንት ማምሻውን በለንደን ስታዲየም በተካሄደው ጨዋታ ቫለንቲን ካስቴላኖስ እና ኮንስታንቲኖስ ማቭሮፓኖስ በተመሳሳይ ሁለት ግቦችን አስቆጥረዋል።
ዌስትሃም ዩናይትድ ኢላማቸውን የጠበቁ የግብ እድሎችን በመፍጠር የተሻለ ነበር።
ተጋጣሚው ዎልቭስ የኳስ ቁጥጥር ብልጫውን ትርጉም ወዳላቸው የግብ እድሎች መቀየር አልቻለም።
በሊጉ ስምንተኛ ድሉን ያስመዘገበው ዌስትሃም ዩናይትድ በ32 ነጥብ ደረጃውን ከ18ኛ ወደ 17ኛ ከፍ በማድረግ ከወራጅ ቀጠና ወጥቷል። ወሳኝ ሶስት አሳክቷል።
ጨዋታው ለዌስትሃም ዩናይትድ ደጋፊዎች አስደሳች ሆኖ አልፏል።
ውጤቱን ተከትሎ ቶተንሃም ሆትስፐርስ በ30 ነጥብ ወደ 18ኛ ደረጃ ዝቅ በማለት ወራጅ ቀጠና ገብቷል።
የሰሜን ለንደኑ ክለብ ወራጅ ቀጠና ሲገባ ከ17 ዓመታት በኋላ ለመጀመሪያ ጊዜ ነው።
በሊጉ 21ኛ ሽንፈቱን ያስተናገደው ዎልቭስ በ17 ነጥብ የመጨረሻውን 20ኛ ደረጃ ይዟል።
ዎልቭስ ከእንግሊዝ ፕሪሚየር ሊግ ለመውረድ ተቃርቧል።
ከሶስት ሳምንታት በኋላ የእንግሊዝ ፕሪሚየር ሊግ በ32ኛ ሳምንት የተመለሰ ሲሆን እስከ ሚያዚያ 5 ቀን 2018 ዓ.ም ይቆያል።