የሊጉ መሪ አርሰናል ከቦርንማውዝ ይጫወታል - ኢዜአ አማርኛ
የሊጉ መሪ አርሰናል ከቦርንማውዝ ይጫወታል
አዲስ አበባ፤ ሚያዚያ 3/2018 (ኢዜአ)፦ በእንግሊዝ ፕሪሚየር ሊግ 32ኛ ሳምንት ሁለተኛ ቀን ውሎ አራት ጨዋታዎች ይካሄዳሉ።
ከቀኑ 8 ሰዓት ከ30 አርሰናል ቦርንማውዝን በኤምሬትስ ስታዲየም ያስተናግዳል።
አርሰናል በ70 ነጥብ ሊጉን እየመራ ነው። ቦርንማውዝ በ42 ነጥብ 13ኛ ደረጃ ላይ ይገኛል።
የሰሜን ለንደኑ ክለብ ካሸነፈ መሪነቱን አጠናክሯል። ከተከታዩ ማንችስተር ሲቲ ጋር ያለው የነጥብ ልዩነት ወደ 12 ያሰፋል።
ቦርንማውዝ ባለፉት 11 የሊግ ጨዋታዎች አላሸነፈም። ቡድኑ ባለፉት አምስት ተከታታይ የሊግ ጨዋታዎች አቻ ወጥቷል።
ክለቡ ለመጨረሻ ጊዜ በሊጉ ያሸነፈው በ26ኛ ሳምንት ሲሆን በወቅቱ ኤቨርተንን 2 ለ 1 ረቷል።
በሌላኛው መርሐ ግብር ሊቨርፑል ከፉልሃም ምሽት 1 ሰዓት ከ30 ላይ በአንፊልድ ሮድ ስታዲየም ጨዋታቸውን ያደርጋሉ።
የወቅቱ የሊጉ አሸናፊ ሊቨርፑል በ49 ነጥብ አምስተኛ ደረጃን ይዟል። ፉልሃም በ44 ነጥብ ዘጠነኛ ደረጃ ላይ ተቀምጧል።
የመርሲሳይዱ ክለብ ባለፉት ሶስት የሊግ ጨዋታዎች አላሸነፈም። በ31ኛ ሳምንት በርንሌይን 3 ለ 1 ያሸነፈው ፉልሃም ተከታታይ ድሉን ለማስመዝገብ ይጫወታል።
ጨዋታው ለሁለቱም ቡድኖች በአውሮፓ መድረክ ለመሳተፍ በሚያደርጉት ፉክክር ወሳኝ የሚባል ነው።
ብሬንትፎርድ ከኤቨርተን እና በርንሌይ ከብራይተን በተመሳሳይ ከቀኑ 11 ሰዓት ላይ ይጫወታሉ።