ቀጥታ፡

የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል መንግስት ለ625 የሕግ ታራሚዎች ይቅርታ አደረገ

ወላይታ ሶዶ ፤ ሚያዝያ 2/2018 (ኢዜአ)፦በደቡብ ኢትዮጵያ ክልል የትንሣኤ በዓልን ምክንያት በማድረግ ለ625 የሕግ ታራሚዎች ይቅርታ መደረጉን የክልሉ ርዕሰ መስተዳድር ጥላሁን ከበደ ገለጹ።

የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ርዕሰ መስተዳድር ጥላሁን ከበደ፤ በዓሉን ምክንያት በማድረግ ለታራሚዎች የተደረገውን ይቅርታ በተመለከተ መግለጫ ሰጥተዋል። 

በመግለጫቸውም በማረሚያ ቤት ቆይታቸው መልካም ሥነ-ምግባር የነበራቸው እና በሕግ በተደነገገው መሰረት የይቅርታ መስፈርት ያሟሉ ታራሚዎች በአሰራሩ መሰረት ይቅርታ ተደርጎላቸዋል ብለዋል።

የይቅርታው ተጠቃሚዎች ይቅርታ የማያስከለክል ወንጀል ፈፅመው የነበሩ፤ ከተፈረደባቸው አንድ ሶስተኛ እና ከግማሽ  በላይ የፍርድ ጊዜያቸውን ያጠናቀቁ ስለመሆናቸውም አስረድተዋል።

የይቅርታው ተጠቃሚዎች ከተጎጂ ወገኖች ጋር ታርቀው የእርቅ ሰነድ ማቅረባቸው የተረጋገጠ መሆኑንም ተናግረዋል።    

በመሆኑም አሰራሩን በመከተል በክልሉ የይቅርታ ቦርድ ተጣርቶ በቀረበው መሰረትም ለ625 የሕግ ታራሚዎች ይቅርታ የተደረገላቸው መሆኑን ገልጸዋል።

የይቅርታው ተጠቃሚዎች በቀጣይ ህይወታቸው ሰላም ወዳድ፣ ለሕግ ተገዥና አምራች ዜጋ በመሆን እንዲያገለግሉ ርእሰ መስተዳድሩ ምክራቸውን ለግሰዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም