ቀጥታ፡

ስቅለትን ስናከብር ለበደሉን ይቅርታን በመለገስና ለተቸገሩ ወገኖች ፍቅርና ልግስናን በመስጠት ሊሆን ይገባል

አዲስ አበባ፤ ሚያዝያ 2/2018 (ኢዜአ)፦የኢየሱስ ክርስቶስን የስቅለት በዓል ስናከብር፤ እርስ በርስ በመዋደድ፣ ለበደሉን ይቅርታን በመለገስና ለተቸገሩ ወገኖች የፍቅር እጃችንን በመዘርጋት ሊሆን ይገባል ሲሉ ኢዜአ ያነጋገራቸው የሃይማኖት አባቶችና የእምነቱ ተከታዮች ገለፁ።

በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተ ክርስቲያን በመንበረ ጸባኦት ቅድስት ሥላሴ ካቴድራል የቤተ ክርስቲያኗ ፓትርያርክ ብጹዕ ወቅዱስ አቡነ ማትያስ፣ ብጹዓን ሊቃነ ጳጳሳት፣ የሃይማኖት አባቶች እና ምዕምናን በተገኙበት የኢየሱስ ክርስቶስ ስቅለት በተለያዩ ሃይማኖታዊ ስርዓቶች ተከብሯል።

በዓሉ ኢየሱስ ክርስቶስ ለሰው ልጆች መዳን ብሎ የከፈለውን መከራ፣ ግርፋትና ስቅላት በማሰብ በስግደት፣ በጸሎትና ሌሎች ሃይማኖታዊ ስርዓቶች  ነው የተከበረው።

ኢዜአ ያነጋገራቸው የሃይማኖት አባቶችና የእምነቱ ተከታዮች የስቅለት በዓል ይቅርታና ፍቅር የተገለጠበት መሆኑን ተናግረዋል።

እለቱን ስናስብ የበደሉንን ይቅር በማለት ዕርቅ በማድረግና በፍቅር በመመላለስ ሊሆን ይገባል ነው ያሉት።


 

የመንበረ ጸባኦት ቅድስት ሥላሴ ካቴድራል ሰባኬ ወንጌል በቃሉ ሞላ እንደተናገሩት፥ ኢየሱስ ክርስቶስ በስቅለቱ ለሰው ልጆች ፍጹም ፍቅርን፣ ትህትናንና ይቅርታን አስተምሯል።

"ፈጣሪ የሰውን ልጅ ያለ ዋጋ የወደደበት፣ መከራን የተቀበለበት የፍቅር ጥግ የታየበት እለት ነው" ሲሉ ሃይማኖታዊ ይዘቱን አብራርተዋል።

የዕምነቱ ተከታዮች ስቅለትን ሲያስቡ ኢየሱስ ክርስቶስ ያደረገላቸውን ፍጹም ፍቅርና ይቅርታ በመገንዘብ የተቸገሩትን መርዳት፣ መተባበርና እርስ በርስ መዋደድ እንዳለባቸው አስረድተዋል።

በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተ ክርስቲያን ሰባኬ ወንጌል ቀሲስ አየነ፥ ኢየሱስ ክርስቶስ ለሰው ልጆች ያሳየውን ፍጹም ፍቅር ምዕመናን እርስ በርሳቸው በመዋደድና መልካምነትን በመተግበር ሊያሳዩ ይገባል ብለዋል።


 

በመሆኑም የስቅለት በዓልን ስናከብር ቂምና ጥላቻን በማስወገድ እና የተቸገሩ ወገኖችን በመደገፍ  መሆን አለበት ነው ያሉት።

የመንበረ ጸባኦት ቅድስት ሥላሴ ካቴድራል ምክትል ዋና ፀሐፊ መጋቤ ሥርዓት ፍሬው ፈንታ በበኩላቸው፤ በስቅለት ዕለት የሚከናወነው የስግደት፣ የፀሎትና ምህላ መርሃ-ግብር ክርስቶስ ለሰው ልጆች ነፃ መውጣት የከፈለውን ዋጋ በማሰብ ነው ብለዋል።


 

በዓሉ እርስ በርስ በመዋደድ አንድነትን ማጠናከርን እንደሚያስተምርም ተናግረዋል።

በመንበረ ጸባኦት ቅድስት ሥላሴ ካቴድራል የስቅለት በዓል አከባበር ላይ ያገኘናቸው ምዕመናን በበኩላቸው፤ የስቅለት በዓል ክርስቶስ ለሰው ልጆች ሁሉ ታላቅ ፍቅርን የገለጠበት እንደሆነ ገልጸዋል።

በዓሉን ስናከብር እርስ በርስ ይቅር በመባባል፣ የተቸገሩትን በመርዳት፣ ፍጹም ፍቅርና ልግስናን በመስጠትና በመተባበር መሆን ይገባል ሲሉም አስተያየታቸውን ሰጥተዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም