በድሬዳዋ በሸቀጦች ላይ ያልተገባ የዋጋ ጭማሪ እንዳይደረግ ቁጥጥር እየተደረገ ነው - ኢዜአ አማርኛ
በድሬዳዋ በሸቀጦች ላይ ያልተገባ የዋጋ ጭማሪ እንዳይደረግ ቁጥጥር እየተደረገ ነው
ድሬደዋ ፤ ሚያዝያ 2/2018 (ኢዜአ)፦ በአልን ምክንያት በማድረግ በሸቀጦች ላይ ያልተገባ የዋጋ ጭማሪ እንዳይደረግ ቁጥጥርና ክትትል እየተደረገ መሆኑን የድሬዳዋ አስተዳደር ገለፀ።
ሸማቾች በበኩላቸው ለትንሳኤ በዓል የግብርናና የኢንዱስትሪ ውጤቶችን በተመጣጣኝ ዋጋ እየገዙ መሆናቸውን ተናግረዋል።
የድሬዳዋ አስተዳደር ንግድ ፅህፈት ቤት ኃላፊ አቶ አሚኖ ጣሃ ለኢዜአ እንደገለፁት ፤ የነዳጅ እጥረትና በአልን ምክንያት በማድረግ በግብርናና በኢንዱስትሪ ምርቶች ላይ ያልተገባ የዋጋ ጭማሪ የሚያደርጉ አካላትን በህግ ተጠያቂ ለማድረግ ግብረ ኃይል ተቋቁሞ ወደ ስራ ተገብቷል።
ግብረ ሀይሉ ከህብረተሰቡ በሚደርሰው ጥቆማና መረጃዎች መሰረት የኢንዱስትሪ ምርቶች ላይ ያልተገባ የዋጋ ጭማሪ በማያደርጉና እጥረት ለመፍጠር የሚፈልጉ አካላትን በህግ ተጠያቂ እያደረገ መሆኑን ተናግረዋል።
ያልተገባ ጥቅም ለማግኘት የሚፈልጉ ጥቂት ነጋዴዎች ወቅታዊ ሁኔታን በመጠቀም በህዝቡ ላይ የሚያደርሱትን ጫና ለመከላከል ጠንካራ ክትትል እየተደረገ ይገኛል ብለዋል።
ከዚህ ጎን ለጎን ግብረ ኃይሉ የልኳንዳ ቤቶች የትንሳኤ በአልን ምክንያት በማድረግ በስጋ ዋጋ ላይ ጭማሬ እንዳያደርጉ መግባባት ላይ መደረሱን አቶ አሚኖ ገልጸዋል ።
በማህበራትና ዩኒየኖች እንዲሁም በባዛሮችና በቅዳሜና እሁድ ገበያዎች በኩል ለትንሳኤ በአል የፍጆታ ምርቶች በበቂ ሁኔታ መቅረባቸውንም አስታውቀዋል ።
በቅዳሜና እሁድ ገበያ እና ለበዓል በተዘጋጀው የንግድ ባዛር ላይ ምርቶችን ሲሸምቱ የነበሩት ወይዘሮ ትርሲት ጌታቸው እና ወይዘሮ ትቅደም አሰፋ ለበዓል በቂ የግብርና እና የኢንዱስትሪ ምርቶች መቅረባቸውን ተናግረዋል።
ምርቶቹን በተመጣጣኝ ዋጋ መግዛታቸውን ጠቅሰው አስተዳደሩ እያደረገ የሚገኘውን ቁጥጥርና ክትትል ማጠናከር እንዳለበት ገልጸዋል ።
በምርቶች ላይ ያልተገባ የዋጋ ጭማሬ የሚያደርጉ ነጋዴዎች ተጠያቂ እንዲሆኑ የድርሻቸውን እንደሚወጡ ተናግረዋል።