የሊጉ መሪ ሲዳማ ቡና በመቻል ተሸነፈ - ኢዜአ አማርኛ
የሊጉ መሪ ሲዳማ ቡና በመቻል ተሸነፈ
አዲስ አበባ፤ ሚያዝያ 2/2018 (ኢዜአ)፦ በኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ የ26ኛ ሳምንት ተጠባቂ መርሐ ግብር መቻል ከመመራት ተነስቶ ሲዳማ ቡናን 3 ለ 1 አሸንፏል።
በሃዋሳ ዩኒቨርሲቲ ስታዲየም በተካሄደው ጨዋታ ፍቅረየሱስ ተክለብርሃን በ28ኛው ደቂቃ ባስቆጠረው ግብ ሲዳማ ቡና መሪ ሆኗል።
ቸርነት ጉግሳ በ40ኛው፣ ግሩም ሃጎስ በ51ኛው እና በረከት ደስታ በ88ኛው ደቂቃ ከመረብ ላይ ያሳረፏቸው ጎሎች መቻልን አሸናፊ አድርጓል።
ከሶስት የአቻ ውጤቶች በኋላ ወደ አሸናፊነት የተመለሰው መቻል በ40 ነጥብ ደረጃውን ከስድስተኛ ወደ አራተኛ ከፍ አድርጓል። በሊጉም ዘጠነኛ ድሉን አስመዝግቧል።
በአንጻሩ በሊጉ አራተኛ ሽንፈቱን ያስተናገደው መሪው ሲዳማ ቡና 48 ነጥብ ላይ ረግቷል።
ከተከታዩ ነገሌ አርሲ ጋር ያለውን የነጥብ ልዩነት ወደ ዘጠኝ ከፍ የማድረግ እድል ሳይጠቀምበት ቀርቷል።
ዛሬ በተደረገ ሌላኛው ጨዋታ ባህር ዳር ከተማ አዳማ ከተማን 2 ለ 1 አሸንፏል።
ጨዋታዎቹን ተከትሎ 26ኛ ሳምንት ተጠናቋል።
የ27ኛ ሳምንት መርሐ ግብር ከሰኞ ሚያዚያ 5 ቀን 2018 ዓ.ም አንስቶ እንደሚካሄድ የሊጉ አክሲዮን ማህበር አስታውቋል።