ቀጥታ፡

በከተሞቹ በትንሳዔ በዓል ገበያ በቂ ምርትና የእርድ እንስሳት ቀርቧል 

ሆሳዕና ፤ ሚያዝያ 2/2018 (ኢዜአ)፦በሆሳእና፣ ወላይታ ሶዶና ቦንጋ ከተሞች በትንሳዔ በዓል ገበያ በቂ የምርትና የእርድ እንስሳት አቅርቦት መኖሩ ተመለከተ።

በሆሳእና ከተማ በትንሳኤ በአል ገበያ የፍጆታ ምርቶችና የእርድ እንስሳት በተመጣጣኝ ዋጋ  ግብይት እየተካሄደ መሆኑን ሸማቾችና ነጋዴዎች ገልጸዋል።

በከተማው ሄጦ ቀበሌ ነዋሪ ወይዘሮ አልማዝ ዘውዴ ለበዓሉ የሚሆናቸውን ዶሮ በተመጣጣኝ ዋጋ መግዛታቸውን ተናግረዋል።

በገበያው የምርትና የእርድ እንስሳት አቅርቦት በበቂ ሆኔታ መኖሩን የገለጹት ደግሞ በከተማው በሊች አምባ ቀበሌ ነዋሪ አቶ ተመስገን ታደሰ ናቸው ። 

ለበዓሉ የሚሆናቸውን ፍየል እንደ አቅማቸው መግዛታቸውን ተናግረዋል።


 

በገበያው የምርት አቅርቦቱ በአማራጭ መቅረብ በመቻሉ ሁሉም አቅሙን ባገናዘበ መልኩ ሸምቶ በዓሉን እንዲያከብር አስቻይ ሁኔታ ስለመፈጠሩም አመልክተዋል።

በከተማው በቅመማ ቅመም ንግድ ዘርፍ የተሰማሩት አቶ አክሊሉ ዘውዴ እንደገለፁት፤ ለበዓሉ የሚያስፈልጉ ሽንኩርትን ጨምሮ ሌሎች የቅመማ ቅመም ምርቶች ላይ የዋጋ ጭማሪ አለመደረጉን ተናግረዋል።

ምርቶቹን ከተለያዩ የንግድ ማህበራት በዓሉ ከመድረሱ አስቀድመው ማግኘት በመቻላቸው በተመጣጣኝ ዋጋ እየሸጡ መሆናቸውን ተናግረዋል።

በዞኑ የትንሳኤ በዓልን ምክንያት በማድረግ ሊከሰት የሚችልን ተገቢ ያልሆነ የዋጋ ጭማሪ ለመከላከል የሚያስችል ግብረ ኃይል ተቋቁሞ ወደ ተግባር መገባቱን የተናገሩት ደግሞ የሀድያ ዞን ንግድና ገበያ ልማት መምሪያ ኃላፊ አቶ ተከተል ዶባሞ ናቸው፡፡

ለበዓሉ የሚሆኑ የመሰረታዊና የፍጆታ ምርቶች አቅርቦት ውስንነት እንዳይኖር ከተለያዩ በንግድ ዘርፍ ከተሰማሩ ማህበራት ጋር ትስስር በመፍጠር ምርቱ እንዲቀርብ ስለመደረጉ ተናግረዋል፡፡

እንዲሁም ለበዓሉ የሚሆን የእርድ እንሰሳትም ጭምር በስፋት እንዲቀርብ ተደርጎ ማህበረሰቡ በተመጣጣኝ ዋጋ ሸምቶ በዓሉን እንዲያከብር ተገቢው ድጋፍና ክትትል እየተደረገ መሆኑን አስታውቀዋል።

በተመሳሳይ በወላይታ ሶዶ ከተማ በትንሳኤ በአል ገበያ ምርትና የእርድ እንስሳት በቂ አቅርቦት መኖሩን ነዋሪዎች ገልጸዋል።


 

የከተማው ነዋሪ ወይዘሮ አምሳል አድነው እንደገለጹት፤ በከተማው በግብይት ማዕከላት እና በመደበኛ የገበያ ስፍራዎች የተሻለ አቅርቦት በመኖሩ እንደየአቅማቸው የመገበያየት ዕድል አግኝተዋል።

ነጭና ቀይ ሽንኩርት እንዲሁም  ዘይትና የዳቦ ዱቄት በተመጣጣኝ ዋጋ መግዛታቸውን ጠቅሰዋል ።


 

አቶ እንድሪያስ ኦይዳ በበኩላቸው፤ ዶሮ እንዲሁም  የበግና የፍየል  አቅም በሚፈቅደው ልክ ግብይት እየተካሄደ መሆኑን ተናግረዋል ።

በከተማው በሰንጋ ገበያ በቂ አቅርቦት መኖሩን ጠቁመው ይሁንና ካለፈው በአል መጠነኛ የዋጋ ጭማሪ መኖሩን አመልክተዋል ።

በዞኑ ባሉ ሁሉም አካባቢዎች ከሸማቾች ህብረት ስራ ዩኒየን እና ማህበራት ጋር በመቀናጀት የተለያዩ የግብርና እና የኢንዱስትሪ ምርቶችን በማቅረብ ለህብረተሰቡ ተደራሽ እየተደረገ ነው ያሉት ደግሞ የወላይታ ዞን ንግድና ኢንዱስትሪ ልማት መምሪያ ኃላፊ ወይዘሮ ወይንሸት ሞላ ናቸው።


 

በተመሳሳይ በቦንጋ ከተማም በትንሳኤ በአል ገበያ በቂ የፍጆታ ምርቶችና የእርድ እንስሳት አቅርቦት መኖሩን ሸማቾች ገልጸዋል ።

መምህር ማቲዎስ ሳህሌና አቶ መሠረት ተረፈ የዘንድሮ የፋሲካ በዓል ገበያ የተረጋጋ መሆኑን ገልጸው እንደየ አቅማቸው መሸመታቸውን ተናግረዋል።


 

የካፋ ዞን ንግድና ኢንቨስትመንት መምሪያ ምክትል ኃላፊ አቶ ሀብታሙ ገብረ ስላሴ  በበኩላቸው፤ በትንሳኤ በዓል ገበያ የፍጆታ ዕቃዎች እጥረት እንዳይኖር በሸማቾች ሕብረት ስራ ማህበራትና በቅዳሜና እሁድ ገበያዎች በኩል በቂ ምርት መቅረቡን  አስታውቀዋል።  

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም