የኢየሱስ ክርስቶስን ስቅለት ስናስብ በይቅር ባይነትና ፍጹም ፍቅር በመስጠት ሊሆን ይገባል-ብፁዕ ካርዲናል ብርሀነ ኢየሱስ ሱራፌል - ኢዜአ አማርኛ
የኢየሱስ ክርስቶስን ስቅለት ስናስብ በይቅር ባይነትና ፍጹም ፍቅር በመስጠት ሊሆን ይገባል-ብፁዕ ካርዲናል ብርሀነ ኢየሱስ ሱራፌል
አዲስ አበባ፤ ሚያዝያ 2/2018 (ኢዜአ)፦የኢየሱስ ክርስቶስን ስቅለት ስናስብ እርስ በርሳችን ይቅርታ በማድረግና ፍጹም ፍቅር በመስጠት ሊሆን ይገባል ሲሉ የኢትዮጵያ ካቶሊካዊት ቤተክርስቲያን ሊቀ ጳጳስ ብፁዕ ካርዲናል ብርሀነ ኢየሱስ ሱራፌል ገለጹ።
የስቅለት በዓል በልደታ ማሪያም ካቶሊክ ካቴድራል ቤተክርስቲያን በርካታ ምዕመናን በተገኙበት በተለያዩ ሃይማኖታዊ ሥነ-ሥርዓቶች ታስቧል።
ብፁዕ ካርዲናል ብርሃነ ኢየሱስ ሱራፌል በዚሁ ወቅት፣ የስቅለት በዓል ኢየሱስ ክርስቶስ ለሰው ልጅ ድኅነት ሲል የደረሰበትን ግርፋት፣ ስቃይ፣ መከራና በመስቀል ላይ መቸንከሩን የምናስታውስበት ነው ብለዋል።
ኢየሱስ ክርስቶስ በስቅለቱና በሞቱ የሰውን ልጅ አድኗል ያሉት ብፁዕ ካርዲናሉ፥ በመስቀሉ ላይ ሆኖ የሚያደርጉትን አያውቁምና ይቅር በላቸው ብሎ ይቅርታን ማስተማሩንም አስረድተዋል።
ዕለቱ እኛም የበደሉንን ይቅር ብለን፣ ለእርቅና በሰላም የምንጸልይበት ቀን ነው ብለዋል።
ምዕመኑ በዚህ ቀን በፆም፣ በጸሎት፣ በስግደት እና ንስሐ በመግባት ከጌታው ጋር እርቅ የሚያወርድበት መሆኑንም አስገንዝበዋል።
ሁላችንም በሰራነው ሀጢያት በማዘንና ፈጣሪን ይቅርታ በመለመን፣ እርስ በርስ በመተሳሰብ፣ በመፋቀርና የተጎዱትን በማሰብ በዓሉን ማክበር ይገባል በማለትም መልዕክታቸውን አስተላልፈዋል።
በልደታ ማርያም ካቶሊካዊት ቤተክርስቲያን አገልጋይ የሆኑት ገብሩ ሀብተ ዮሃንስ፤ የሰው ልጅ እውነተኛ ፍቅርና ሰላም የሚገኙት ከፈጣሪ ዘንድ መሆኑን አስረድተዋል።
ምዕመኑም በዚህ የስቅለት ዕለት በፈጣሪ ፊት ዝቅ በማለትና ይቅርታን በመለመን በመንፈሳዊ ተግባራት እንደሚያሳልፉ ገልጸዋል።
በልደታ ማርያም ካቶሊካዊት ካቴድራል ቤተክርስቲያን የተገኙ የእምነቱ ተከታይ አቶ ማስረሻ አውላቸው እና ረድኤት ገብሩ፥ በዓሉ የኢየሱስ ክርስቶስን ፍጹም ትህትና የምናይበት ነው ብለዋል።
በመሆኑም ክርስቲያኖች ከዚህ ታላቅ ትምህርት በመነሳት ለሌሎች ሰዎች መልካምነትንና መተሳሰብን በተግባር ማሳየት አለብን ነው ያሉት።
ኢየሱስ ክርስቶስ ለሰው ልጅ መዳን ሲል የከፈለውን መለኮታዊ ዋጋ አርዓያ በማድረግ፣ መልካምነትን በተግባር በመግለጽ የሕይወት መመሪያ ማድረግ እንደሚገባም ጠቅሰዋል።