ቀጥታ፡

ኢትዮጵያ በዲጂታል ዘርፍ ያሳየችው ፈጣን ሽግግር እና ያስመዘገበችው ውጤት ለአህጉሪቱ  ምሳሌ ነው

አዲስ አበባ፤ሚያዝያ 2/2018 (ኢዜአ)፦ኢትዮጵያ በዲጂታል ዘርፍ  ያሳየችው ፈጣን ሽግግርና ያስመዘገበችው ውጤት ለአህጉሪቱ  ምሳሌ  መሆኑን በአፍሪካ ስታትስቲክስ ኢንስቲትዩት የኢኮኖሚ ስታትስቲክስ ዳይሬክቶሬት ኃላፊ አዱም ጋጎሉም ገለጹ።

ኃላፊው ከኢዜአ ጋር ባደረጉት ቆይታ እንደገለጹት፣ ከአህጉሪቱ ጠቅላላ የሀገር ውስጥ ምርት 65 በመቶውን አስተዋጽኦ የሚያደርገውን መደበኛ ያልሆነ የኢኮኖሚ ዘርፍ ለመደገፍ ዲጂታላይዜሽን ወሳኝ ነው።


 

በኢትዮጵያ በሚሊዮን የሚቆጠሩ ዜጎችን የፋይናንስ ተጠቃሚ ያደረጉት እንደ ቴሌ ብር እና ሲቢኢ ብር ያሉ የቴክኖሎጂ ውጤቶች በአጭር ጊዜ ውስጥ ያመጡት ለውጥ እጅግ አስደናቂና አበረታች መሆኑን በምሳሌነት ጠቅሰዋል።

ኢትዮጵያ የአርቲፊሻል ኢንተለጀንስ ዩኒቨርሲቲ ለመክፈት የጀመረችው ስራ ለአህጉሪቱ አዲስ ተስፋ የሚሰጥ መሆኑንም አንስተዋል።

ኢትዮጵያ ተግባራዊ ያደረገችው ሀገር በቀል የኢኮኖሚ ሪፎርም እና የማክሮ ኢኮኖሚ ማሻሻያ ፖሊሲዎች ተጨባጭ ውጤት እያመጡ መሆኑንም ተናግረዋል።

በተለይም ዓለም አቀፋዊ ተወዳዳሪነትን ለማስፈን እንደ ቴሌኮም እና ባንክ ያሉ ቁልፍ ዘርፎች ለውጭ ኢንቨስትመንት ክፍት መደረጋቸው የሀገሪቱን የሊብራላይዜሽን ጉዞ የሚያፋጥን ትክክለኛ ውሳኔ ነው ብለዋል።

የተመዘገቡት የልማት ስኬቶችና የመሰረተ ልማት ግንባታዎች፣ በፈረንጆቹ 2063  የበለጸገች አፍሪካን እውን ለማድረግ ትልቅ ሚና እንደሚኖራቸው አስገንዝበዋል። 

ኢትዮጵያ እያሳየች ያለው ፈጣን ለውጥ በሌሎች የአፍሪካ ሀገራት ከቀጠለ፣ አፍሪካ በዓለም አቀፍ መድረክ ያላትን ተሰሚነትና ክብር ከፍ እንደሚያደርገው አብራርተዋል።


 

የዓለም አቀፍ የገንዘብ ድርጅት (IMF) የስታትስቲክስ ዲፓርትመንት ምክትል ዳይሬክተር ጂም ቴብራክ፣ ዲጂታላይዜሽን የፋይናንስ ተደራሽነትን በማስፋት ለዓለም ኢኮኖሚ ትራንስፎርሜሽን ከፍተኛ አስተዋጽኦ እያበረከተ ይገኛል ብለዋል።።

በኢትዮጵያ በዲጂታላይዜሽን መስፋፋት እየታየ ያለው እንቅስቃሴ በጥሩ ደረጃ ላይ እንደሚገኝ አመልክተዋል።

በአሁኑ ወቅት ዓለም በሰው ሰራሽ አስተውሎት ዘመን ላይ በመሆኗ፣ ሀገራት በጤና፣ በትምህርትና በንግድ ዘርፎች ተጠቃሚ ለመሆን አስፈላጊውን ዝግጅት ማድረግ እንዳለባቸውም አጽንኦት ሰጥተዋል።

ይህ የዲጂታል ለውጥ የፋይናንስ አገልግሎት ባልደረሰባቸው አካባቢዎች ጭምር ቀላልና ፈጣን አማራጮችን በማስፋፋት፣ ሁሉን አቀፍ የኢኮኖሚ ዕድገት ለማምጣት ቁልፍ ሚና እንደሚጫወት ነው ያብራሩት።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም