ቀጥታ፡

በጀጎል ግንብ ውስጥ የሚገነባው የ”ዳር ሀረር” የመልሶ ማልማት ፕሮጀክት ግንባታ ሊጀመር ነው

አዲስ አበባ፤ሚያዝያ 2/2018 (ኢዜአ)፦ የሀረሪ ክልል መስተዳድር ምክር ቤት በጀጎል አለም አቀፍ ቅርስ ውስጥ የሚገነባው የ''ዳር ሀረር'' መልሶ ማልማት ፕሮጀክት ግንባታ በአፋጣኝ ወደ ስራ ማስገባት በሚቻልባቸው ጉዳዮች ውይይት አድርጓል።

ፕሮጀክቱ በአለም ቅርስነት የተመዘገበው የጀጎል አለም አቀፍ ቅርስን ለነዋሪውና ለጎብኚዎች የበለጠ ምቹ ለማድረግ የሚያግዝ ስለመሆኑ ተገልጿል።

በውይይቱ ላይም የ''ዳር ሀረር'' የመልሶ ማልማት ፕሮጀክት የሀገር ኩራት ከሆነው የጀጎል አለም አቀፍ ቅርስ ታሪክና ይዘት ጋር በማጣጣምና የጀጎል ባህላዊ የግንባታ ጥበብን በተከተለ መልኩ እንደሚከናወን የክልሉ ኮሙኒኬሽን ቢሮ አስታውቋል።


 

የሚገነባው የ''ዳር ሀረር'' የመልሶ ማልማት ፕሮጀክትም በቅርሱ ውስጥ የሚገኙ ነዋሪዎችን ህይወት ለማሻሻል የሚያግዝ መሆኑ ተጠቅሷል።

ፕሮጀክቱ የህዝብን ተጠቃሚነት ከማሳደግም ባሻገር የሀረርን ከፍታ ለማረጋገጥ በሚሰሩ ስራዎች የጎላ ፋይዳ እንዳለው ነው የተመላከተው።

በፕሮጀክቱም ዘመናዊ አገልግሎት የሚሰጡ ታሪካዊ ይዘታቸውን የጠበቁ የቱሪስት ማረፊያዎች ይገነባሉ ተብሏል።

ፕሮጀክቱ ሲጠናቀቅም ሀረርን በምስራቅ አፍሪካ ቀዳሚ የቅርስ ቱሪዝም መዳረሻ በማድረግ ረገድ ከፍተኛ ሚና እንደሚኖረው ቢሮው በመረጃው አመልክቷል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም