ቀጥታ፡

የትንሳዔ በዓልን ያለንን በማካፈልና በመረዳዳት በድምቀት ለማሳለፍ ተዘጋጅተናል

አዲስ አበባ፤ሚያዝያ 2/2018 (ኢዜአ)፦የትንሳኤ በዓልን ያለንን በማካፈልና በመረዳዳት በድምቀት ለማሳለፍ ተዘጋጅተናል ሲሉ የመዲናዋ ነዋሪዎች ገለጹ።

በክርስትና እምነት ተከታዮች ዘንድ ከሚከበሩ ዓበይት በዓላት መካከል፣ የኢየሱስ ክርስቶስ የትንሳዔ በዓል አንዱ ነው።

የትንሳዔ በዓል ዋዜማ በየአካባቢው በደመቀ ድባብ ተጀምሯል። የመዲናዋ ነዋሪዎች ወደ ገበያ በመውጣት የሚፈልጉትን እየሸመቱ ናቸው። 

በዓሉን በቤታቸው፣ በአካባቢያቸው እንዲሁም ከመላው ማህበረሰብ ጋር እንዴት ሊያከብሩት እንደተዘጋጁ ገበያ የወጡ የመዲናዋን ነዋሪዎችን አነጋግረናል።

የመዲናዋ ነዋሪዎችም ለኢዜአ በሰጡት አስተያየት የትንሳኤ በዓልን ያላቸውን በማካፈልና በመደጋገፍ ለማሳለፍ መዘጋጀታቸውን ነው የገለጹት።

የትንሳዔ በዓል እግዚአብሔር ለሰው ልጆች ያለውን ታላቅ ፍቅር በልጁ ሞትና ትንሳዔ የገለጠበት ነው ያሉት ነዋሪዎች፤ ከጎረቤቶቻቸው እና ከአካባቢያቸው ሰዎች ጋር በመተባበር የተቸገሩ ወገኖችን እየደገፍን በዓሉን እናሳልፋለን ብለዋል።

ከአስተያየት ሰጪዎቹ መካከል ወይዘሮ ቱቱ ተስፋዬ እንደገለጹት፣ በዓላት በኢትዮጵያውያን ዘንድ በአብሮነትና ያለውን  ከሌሎች ጋር በማካፈል የሚከበሩ ታላላቅ እሴቶች ናቸው።


 

ስለሆነም የትንሳዔ በዓል ቤት ያፈራውን ከጎረቤቶችና ከሌሎች ወገኖች ጋር በመካፈል፣ የበዓሉን እሴት በመጠበቅ በአንድነትና በሰላም ለማክበር መዘጋጀታቸውን ገልጸዋል።

አቶ ሳምሶን ካሳሁን በበኩላቸው፤ በዓሉ የሰላም፣ የፍቅርና የአንድነት ስለሆነ ካለኝ ላይ ለተቸገሩ ወገኖች በማካፈል በዓሉን በደስታ እንዲያሳልፉ የበኩሌን ለማድረግ ተዘጋጅቻለሁ ብለዋል።


 

ለበዓሉ የሚያስፈልጉ የፍጆታ እቃዎች እንደ ሽንኩርት፣ እንቁላል፣ ቅቤ፣ አይብና ዶሮ በተመጣጣኝ ዋጋ መገኘታቸው የበዓሉን ድባብ ይበልጥ ደማቅ እንዲሆን እያገዛ መሆኑን  ጠቁመዋል።

ወይዘሮ አበባ ብሩ እንደሚሉት፣ የትንሳኤ በዓል በመደጋገፍ፣ በሰላምና በአብሮነት፣ ከቤተሰብ፣ ከጎረቤት ጋር በደስታ ያሳልፋሉ።


 

በተመሳሳይ አቶ ኃይሌ ይርጋ እንደገለጹት፣ የፋሲካ በዓልን ከቤተሰብና ከማህበረሰብ ጋር በደመቀ ሁኔታ ለማክበር ተዘጋጅተዋል።

በዓሉን ከደካሞችና ከችግረኞች ጋር በመካፈል ማክበር ደስታ እንደሚጨምርላቸው ነው የተናገሩት። 


 

ነዋሪዎቹ የትንሳዔ በዓልን ሲያከብሩ ከመደሰት በላይ ለሌሎች ደስታ መፍጠር እንደሚገባ በመግለጽ፣ የመካፈልና የመደጋገፍ ባህል እንዲጠናከር ጥሪ አቅርበዋል። 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም