ቀጥታ፡

ኢትዮጵያ በዓድዋ ድል ያሳየችውን አህጉራዊ ምሳሌነት ዛሬም በልማት እየደገመችው ነው-አፍሪካውያን

አዲስ አበባ፤ሚያዝያ 2/2018 (ኢዜአ)፦ኢትዮጵያ በዓድዋ ድል ያሳየችውን አህጉራዊ ምሳሌነት ዛሬም በልማት እየደገመችው ነው ሲሉ የዓድዋ ድል መታሰቢያን የጎበኙ አፍሪካውያን ገለጹ።

ኢትዮጵያ የጀግንነት ታሪክ  መፍለቂያ ሀገር መሆኗን  በመጥቀስ፥ የዓድዋ ድል መታሰቢያ የኢትዮጵያ ብቻ ሳይሆን የአፍሪካውያንና የመላው ጥቁር ሕዝቦች አኩሪ የታሪክ ዓምድ መሆኑን ጠቅሰዋል።

በኢትዮጵያ አስተናጋጅነት የተካሄደው የ16ኛው የአፍሪካ አደጋ ስጋት አቅም ጉባኤ ተሳታፊዎች የኢትዮጵያና የአፍሪካውያን የጀግንነት የታሪክ ማህደር የሆነውን የዓድዋ ድል መታሰቢያን ጎብኝተዋል። 


 

በጉብኝታቸውም የድል ታሪክ ምስክር የሆኑ ቅርሶችንና የጀግንነት አሻራዎችን የተመለከቱ ሲሆን፣ የድል መታሰቢያው ከሀገር ባለፈ ለአፍሪካ የሚተርፍ ትልቅ ትምህርት የያዘ መሆኑን ገልጸዋል።

የዓድዋ ድል ድህነትን ለማሸነፍና ለአፍሪካ ብልጽግና በትብብር ለመሥራት ትልቅ መነሳሳትን የሚፈጥር መሆኑንም ተናግረዋል።

ከጎብኚዎቹ መካከል ጅቡቲያዊው ኢሳም አብዱልሃኪም በሰጡት አስተያየት፤ ኢትዮጵያ የጀግንነት ታሪክ መፍለቂያ መሆኗን በሙዚየሙ ውስጥ ካየኋቸው ታሪኮች ተረድቻለሁ ብለዋል።

የዓድዋ ድል ኢትዮጵያውያን  ሲተባበሩ ለየትኛውም ፈተና የማይበገሩ መሆናቸውን ያረጋገጠ ደማቅ አሻራ መሆኑንም ተናግረዋል።

ይህም ለሁሉም አፍሪካውያን የአይበገሬነትን ትምህርት የሚሰጥ ነው ብለዋል።

ከዛምቢያ የመጡት መሲ ችሉ በበኩላቸው፤ የዓድዋ ድል መታሰቢያ የጦርነት ድልን የሚዘክር ብቻ ሳይሆን በዚህ ዘመን ለልማት መትጋትን የሚያስተምርና ወኔ የሚያስታጥቅ እንደሆነ ጠቁመዋል።


 

አፍሪካውያን ከዓድዋ ደማቅ ታሪክ ተምረን ከተባበርን፤ ልክ እንደ ጦርነቱ ሁሉ ድህነትንም ድል ማድረግ እንችላለን ነው ያሉት።

በአዲስ አበባ የተመለከቱት ውበትና ዕድገትም ኢትዮጵያ ለአፍሪካ ያላትን ምሳሌነት በተግባር ማሳየቱን ገልጸዋል።

በተመሳሳይ ሱዳናዊው እስማዔል አሊ፤ ዓድዋ ትክክለኛ የአመራር ብቃትና የሕዝብ ቁርጠኝነት የታየበት መሆኑን ገልጸዋል።


 

ኢትዮጵያ በጥንቱ ጀግንነቷ ብቻ ሳይሆን ዛሬም  እያስመዘገበቻቸው በሚገኙ የልማት ስኬቶች ለአፍሪካ አርዓያ ሆና ቀጥላለች ብለዋል።

 

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም