በአሶሳ ከተማ ለበዓል ገበያ የግብርናና የፍጆታ ምርቶች በበቂ ሁኔታ ቀርበዋል - ኢዜአ አማርኛ
በአሶሳ ከተማ ለበዓል ገበያ የግብርናና የፍጆታ ምርቶች በበቂ ሁኔታ ቀርበዋል
አሶሳ፤ ሚያዚያ 2/2018 (ኢዜአ)- በአሶሳ ከተማ ለትንሳኤ በዓል ገበያ የሚሆን በቂ የግብርናና የፍጆታ ምርቶች አቅርቦት መኖሩን ሸማቾች እና አቅራቢዎች ተናገሩ።
በአሶሳ ከተማ የገበያ ማዕከል ኢዜአ ያነጋገርናቸው ሸማቾች እና አቅራቢዎች እንደተናገሩት የወቅቱ የትራንስፖርት ችግር ፈተና ቢሆንም ለበዓሉ የግብርናና የፍጆታ ምርቶች በበቂ ሁኔታ ይገኛሉ።
ለበዓል የሚሆኗቸውን ምርቶች ሲሸምቱ ያገኘናቸው ወይዘሮ ህይወት ሀይሉ እና ወጣት አበበ አዳነ እንደተናገሩት፤ በገበያው በቂ የግብርና ምርቶች ቢኖሩም መጠነኛ የዋጋ ጭማሪ ታይቷል።
ይህም የወቅቱን የትራንስፖርት እጥረት ያገናዘበ በመሆኑ ሁሉም እንደሚረዳው የገለጹት ነዋሪዎቹ፣ በገበያው የተጋነነ የዋጋ ጭማሪ እንዳይኖር በመንግስት የተሰራው ስራ በተመጣጣኝ ዋጋ ለመሸመት እንዳስቻላቸው ተናግረዋል።
በከተማዋ ለበዓሉ የግብርናና የፍጆታ ምርቶች በበቂ ሁኔታ መቅረቡን ጠቁመዋል።
በግብርና ምርቶች አቅርቦት ሥራ ላይ የተሰማሩት ሱራፌል በላይ እና መዝገብ አይኑ በበኩላቸው፤ እስካሁን ለበዓል ተብሎ የተለየ የዋጋ ጭማሪ እንዳልተደረገ ተናግረዋል።
በቂ የምርት አቅርቦት በመኖሩ ሸማቾች በፈለጉት አማራጭ እየተገበያዩ እንደሆነ ጠቅሰው፣ ምርትን የሚደብቁ እና ያለአግባብ የዋጋ ጭማሪ የሚያደርጉ ነጋዴዎች ላይ አስፈላጊውን እርምጃ መውሰድ ይገባል ብለዋል።
የቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል ንግድና ገበያ ልማት ቢሮ ኃላፊ አቶ አስር ኢብራሂም የትንሣኤ በዓልን ምክንያት በማድረግ የዋጋ ንረት እና የምርት አቅርቦት እጥረት እንዳይከሰት ከአምራቾች እና ከማህበራት ጋር በመቀናጀት እየተሰራ መሆኑን ተናግረዋል።
ቢሮው ያለአግባብ የዋጋ ጭማሪ በሚያደርጉ አካላት ላይ እየወሰደ ያለውን እርምጃ አጠናክሮ በመቀጠል የተረጋጋ የገበያ ለመፍጠር ከታችኛው መዋቅር ጋር እየሰራ መሆኑንም ገልጸዋል።
በአሁኑ ወቅትም በክልሉ ለበዓሉ የሚሆኑ በቂ የግብርናና የፍጆታ ምርቶች በተመጣጣኝ ዋጋ እየቀረቡ መሆናቸውን አክለዋል።