ቀጥታ፡

በጋምቤላ ክልል የነዳጅ ግብይትና ስርጭት መመሪያ ተግባራዊ እየተደረገ ነው

ጋምቤላ፤ ሚያዝያ 2/2018 (ኢዜአ) ፦በጋምቤላ ክልል የነዳጅ ግብይትና ስርጭት መመሪያን ተግባራዊ በማድረግ በህዝቡ ላይ ሊደረሱ የሚችሉ ጫናዎችን ለመቀነስ በትኩረት እየተሰራ መሆኑን የክልሉ ንግድና ኢንዱስትሪ ቢሮ አስታወቀ።

በክልሉ የነዳጅ ስርጭትና ግብይት መመሪያ ትግበራን ለማሳለጥና ህገ-ወጥ የነዳጅ ግብይትን ለመቆጣጠር በክልሉ ምክትል ርዕሰ መስተዳድር የሚመራ ግብረ ኃይል ተቋቁሞ እየሰራ መሆኑንም ቢሮው ገልጿል።

የጋምቤላ ክልል ንግድና እንዱስትሪ ቢሮ ኃላፊ አቶ ኮንግ ኩላንግ ለኢዜአ እንደገለጹት በመካከለኛው ምስራቅ የተከሰተውን አለመረጋጋት ተከትሎ በህዝብ ላይ ሊደርስ የሚችለውን ጫና ለመቀነስ እንደ ሀገር የነዳጅ ግብይትና አቅርቦት መመሪያ ተላልፏል።

በክልሉ ለነዳጅ አመላላሽ ቦቴዎች፣ የምግብ ፍጆዎችንና ሸቀጦችን ለሚጭኑና ለህዝብ ትራንስፖርት አገልግሎት ለሚሰጡ ተሽከርካሪዎች ቅድሚያ በመስጠት የማስተናገድ ተግባር እየተከናወነ ይገኛል ብለዋል።

እንዲሁም በግብርና ልማት ስራ የሚሰማሩ ትራክተሮችና ሌሎች ተሽከርካሪዎች እየተስተናገዱ እንደሚገኙም ተናግረዋል።

በክልሉ እየተተገበረ የሚገኘውን ይህንኑ የነዳጅ ስርጭትና ግብይት ለማሳለጥና ህገ-ወጥ የነዳጅ ግብይትን ለመቆጣጠር በክልሉ ምክትል ርዕሰ መስተዳድር የሚመራ ሰባት የፌዴራልና የክልል ተቋማት የተካተቱበት ግብረ-ኃይል ተቋቁሞ እየሰራ መሆኑንም ኃላፊው ገልጸዋል።

የህዝብ ትራንስፖርት አገልግሎት ከሚሰጡ አሽከርካሪዎች መካከል አቶ ጋሻው ተፈራና አብዱልፈታ አህመድ በሰጡት አስተያየት መንግስት ዓለም አቀፋዊ ሁኔታዎችን ታሳቢ በማድረግ ያስተላለፈው የነዳጅ ግብይትና ስርጭት መመሪያ አስፈላጊ መሆኑን ተናግረዋል።

ይሁን እንጂ በማደያዎች ከታሪፍ ጀምሮ የአተገባበር ክፍተቶች መኖራቸውን ጠቁመው በመንግስት የተላለፈ የነዳጅ ስርጭትና ግብይት መመሪያ ሳይሸራረፍ በአግባቡ ስራ ላይ ሊውል ይገባል ብለዋል።

የጋምቤላ ከተማ የስፖርት ነዳጅ ማደያ ተወካይ አቶ አዲሱ አሰፋ እንደገለጹት በማደያቸው ከንግድ ቢሮ በሚሰጠው መመሪያ መሰረት ተሽከርካሪዎችን እያስተናገዱ ይገኛሉ።

ታሪፉን በተመለከተም መንግስት ባወጣው የዋጋ ተመን መሰረት እየሸጡ መሆናቸውን ገልጸዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም