ቀጥታ፡

የሌማት ትሩፋት መርሃ ግብር ከተሞችን ወደ አምራችነት እያሸጋገረ ነው   

ባህር ዳር፤ ሚያዚያ 2/2018 (ኢዜአ)፡- በአማራ ክልል የተተገበረው የሌማት ትሩፋት መርሃ ግብር ከተሞችን ወደ አምራችነት እያሸጋገረ መሆኑን የክልሉ እንስሳትና ዓሳ ሀብት ልማት ቢሮ አስታወቀ።   

በተለይም በእንስሳት ሀብት ልማት የተከናወኑ ተግባራት ነዋሪውን ከሸማችነት ወደ አምራችነት ከማሸጋገር ባለፈ ለትንሳኤ በዓል የተሻለ አቅርቦት እንዲኖር እድል ፈጥሯል ብለዋል።   

ቢሮው የትንሳኤ በዓልን ምክንያት በማድረግ በእንስሳትና የእንስሳት ተዋጽኦ ምርት አቅርቦት ዙሪያ ዛሬ መግለጫ ሰጥቷል።

የቢሮ ሃላፊው ጋሻው ሙጨ (ዶ/ር) እንደገለጹት፤ የሌማት ትሩፋት ከመተግበሩ በፊት ከተሞች ከገጠር የሚመጣው ምርት ተጠቃሚ እንጂ አምራች አልነበሩም።   

ይህንን ልምድ ለመቀየር በተለይም አካባቢን መሰረት ያደረገ የእንስሳት ልማት ስራ በልዩ ትኩረት ሲከናወን መቆየቱን ገልጸዋል።

የከተማ አስተዳደሮች ወጣቶችን በማደራጀት፣ ባለሀብቶችንና ግለሰቦችን በማሳተፍ በእንስሳት ማድለብ፣ በዶሮና በወተት ልማት በማሰማራታቸው ከተሞች አሁን ላይ የራሳቸውን ምርት ማመንጨት ወደሚችሉበት ደረጃ ደርሰዋል ብለዋል።

በከተማና በገጠር በተከናወነ የተቀናጀ ስራ ለዘንድሮው የትንሳኤ በዓል ገበያ በተሻለ መልኩ የእርድ እንስሳት፣ የዶሮ፣ የእንቁላልና የወተት ምርቶች በተዘጋጁ ማዕከላት ለህብረተሰቡ እየቀረቡ ይገኛሉ ነው ያሉት።   

የወተት ምርትም ከክልሉ አልፎ ወደ አዲስ አበባና አጎራባች ክልሎች በስፋት እየቀረበ መሆኑን አስረድተዋል።   

የከተማ አስተዳደሮች ለወጣቶች ቦታና ብድር በማመቻቸት፣ የእንስሳት ሀብት ልማቱ በሌማት ትሩፋት መርሃ ግብር ታግዞ የበለጠ ውጤታማ እንዲሆን ትኩረት ተደርጓል ብለዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም