በጭሮ ከተማ ለትንሳኤ በዓል በቂ የእርድ እንስሳት ቀርቧል - ኢዜአ አማርኛ
በጭሮ ከተማ ለትንሳኤ በዓል በቂ የእርድ እንስሳት ቀርቧል
ጭሮ፤ሚያዝያ 2/ 2018 (ኢዜአ)፡- በኦሮሚያ ክልል ምዕራብ ሀረርጌ ዞን ጭሮ ከተማ ለዘንድሮው የትንሳኤ በዓል በቂ የእርድ እንስሳት አቅርቦት መኖሩን ሸማቾችና ነጋዴዎች ገለጹ።
እንደ ነጋዴዎቹ ገለጻ፤ ለበዓሉ የሚሆኑ የእርድ ሰንጋዎች፣ ፍየሎችና ዶሮዎች በስፋት ለገበያ ቀርበዋል።
በእንስሳት ንግድ የተሰማራው ወጣት አሊ መሐመድ እንደገለጸው፤ ለበዓሉ የሚሆኑ የተለያዩ ደረጃ ያላቸው ሰንጋዎች በየዋጋ አማራጫቸው ቀርበዋል።
በተለይም የእንስሳት አቅርቦት ምንጭ ከሆነው የገለምሶ አካባቢ በቂ ምርት በመኖሩ፣ ለሸማቹ የሚፈልገውን ያህል ማቅረብ መቻሉን ተናግሯል።
ሌላኛው ነጋዴ አቶ ጋዲሳ ደመቀ በበኩላቸው፣ ከተለያዩ አካባቢዎች የተውጣጡ ሰንጋዎችን በተለያየ መጠንና ዋጋ ለገበያ ማቅረባቸውን አረጋግጠዋል።
በገበያው ላይ የሚታየውን የዋጋ ሁኔታ በተመለከተ አስተያየታቸውን የሰጡት አቶ ዋሲሁን ጎሳ፣ ከአቅርቦት አንጻር ችግር ባይኖርም መጠነኛ የዋጋ ጭማሪ መታየቱን ጠቁመዋል።
እንደ በሬው ሁኔታ ዋጋ ቢለያይም ለበዓሉ የተሻለ አቅርቦት መኖሩን ተናግረዋል።
በተመሳሳይ የፍየል ገበያን በተመለከተ አቶ ተከተል ገዙ እንደተናገሩት፣ ባለፉት ቀናት ከነበረው ዋጋ መጠነኛ ጭማሪ ቢታይበትም አቅርቦቱ ግን ጥሩ ነው።
በአጠቃላይ በጭሮ ከተማ የትንሳኤ ገበያ ካለፉት ዓመታት በተለየ መልኩ የእንስሳት አቅርቦት የተሻለ መሆኑን ነጋዴዎች እና ሸማቾች ተናግረዋል።