የትውልድ አጀንዳ የሆነውን የባሕር በር ጥያቄ ለማሳካት ወጣቶች በዕውቀትና በንቃት መሳተፍ አለባቸው-የኢትዮጵያ ወጣቶች ፌዴሬሽን - ኢዜአ አማርኛ
የትውልድ አጀንዳ የሆነውን የባሕር በር ጥያቄ ለማሳካት ወጣቶች በዕውቀትና በንቃት መሳተፍ አለባቸው-የኢትዮጵያ ወጣቶች ፌዴሬሽን
አዲስ አበባ፤ሚያዝያ 2/2018 (ኢዜአ)፦የኢትዮጵያን ብሔራዊ ጥቅም ለማስከበርና የትውልድ አጀንዳ የሆነውን የባሕር በር ባለቤትነት ጥያቄን ከግብ ለማድረስ ወጣቶች በዕውቀትና በንቃት መሳተፍ እንዳለባቸው የኢትዮጵያ ወጣቶች ፌዴሬሽን ገለጸ።
የኢትዮጵያን ፈጣን የኢኮኖሚ ዕድገት ዘላቂ ለማድረግና እየጨመረ የመጣውን የሕዝብ የልማት ፍላጎት ለማሟላት አስተማማኝ የባሕር በር ማግኘት አማራጭ የሌለው ጉዳይ ነው።
ይህንን ብሔራዊ ግብ ለማሳካትም፣መንግሥት ኢትዮጵያ የባሕር በር ባለቤት እንድትሆን የሚያስችሉ ውጤታማ የዲፕሎማሲ ሥራዎችን በስፋት እያከናወነ ይገኛል።
የኢትዮጵያ ወጣቶች ፌዴሬሽን ዓለም አቀፍ የሕዝብ ግንኙነት ኃላፊ አምባሳደር አሌክሳንደር ንጉሴ ለኢዜአ እንደገለጹት፥ የባሕር በር መኖር ለኢትዮጵያ ኢኮኖሚያዊና ማኅበራዊ ዕድገት ወሳኝ ነው።
አምባሳደር አሌክሳንደር አክለውም መንግሥት የባሕር በርን በሚመለከት ለሚያከናውናቸው ዲፕሎማሲያዊ ጥረቶች ስኬታማነት ፌዴሬሽኑ የበኩሉን ሚና ለመወጣት እየሠራ መሆኑን አመልክተዋል።
የወጣቶችን ግንዛቤ የሚያጎለብቱ ተግባራትን እያከናወነ መሆኑን ጠቁመው፣የብሔራዊ ጥቅም አጀንዳን በዘላቂነት ለማሳካት ትውልዱ ትልቅ ኃላፊነት እንዳለበት ጠቅሰዋል።
የኢትዮጵያን ብሔራዊ ጥቅም ለማስከበርና የባሕር በር ባለቤትነት ጥያቄን ከግብ ለማድረስ ወጣቶች በዕውቀትና በንቃት ሊሳተፉ እንደሚገባ ገልጸዋል።
በጉዳዩ ላይ አስተያየታቸውን የሰጡ ወጣቶች በበኩላቸው፣ የባሕር በር ጥያቄ የትውልዱ አጀንዳ መሆኑን ገልጸዋል።
ወጣት አቤኔዘር ኤርሚያስ የባሕር በር ጥያቄያችን በዓለም አቀፍ ደረጃ ተቀባይነት እያገኘ መሆኑን ጠቅሶ፥ አሁንም ተፅዕኖ ፈጣሪ ወጣቶችን በመጠቀም አጀንዳውን ለዓለም ይበልጥ ማስገንዘብ አለብን ብሏል።
ወጣቶች በማህበራዊ ሚዲያ አጫጭር ቪዲዮዎችንና የታሪክ ማጣቀሻዎችን በመጠቀም የኢትዮጵያን የባሕር በር ጥያቄ ተገቢነት ከሕጋዊ፣ ታሪካዊና ተፈጥሯዊ አውዶች አንጻር ማሳወቅ ወሳኝ መሆኑን ጠቅሷል።
በተመሳሳይ ወጣት ሩት ሸዋንቅጣውና ፌቨን ፍቃዱ የባሕር በር ጉዳይ የመንግሥት ብቻ ሳይሆን የሁሉም ዜጋ ጉዳይ እንደሆነ አንስተዋል።
ወጣቱ ሐሳቡን በመግለጽና መንግሥትን በመደገፍ ረገድ ግንባር ቀደም ሚና ሊኖረው እንደሚገባ አስገንዝበዋል።