ቀጥታ፡

የኢትዮጵያ የርምጃ አትሌቲክስ ቡድን ለዓለም ሻምፒዮና ወደ ብራዚል አቀና

አዲስ አበባ፤ ሚያዝያ 2/2018 (ኢዜአ)፦ በደቡብ አሜሪካዊቷ አገር ብራዚል በሚካሄደው የዓለም አትሌቲክስ የርምጃ ውድድር ላይ የሚሳተፈው የኢትዮጵያ ልዑካን ቡድን ዛሬ ጠዋት ወደ ስፍራው ማቅናቱን የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ፌዴሬሽን አስታወቀ።

ለ31ኛ ጊዜ በሚዘጋጀው በዚህ ሻምፒዮና ላይ ከዓለም ዙሪያ የተውጣጡ 333 አትሌቶች ይሳተፋሉ።

በዚህ የዓለም አቀፍ መድረክ ኢትዮጵያን ወክለው ከሚሳተፉ አትሌቶች መካከል በፓሪስ ኦሎምፒክ ተሳትፎው አመርቂ ውጤት ያስመዘገበው አትሌት ምስጋና ዋቁማ በ20 ኪሎ ሜትር የርምጃ ውድድር የሚካፈል ሲሆን፤ በአንጎላ እና ናይጄሪያ በተደረጉ የአፍሪካ ወጣቶች ሻምፒዮናዎች የወርቅ ሜዳሊያ ባለቤት የሆነችው አትሌት ህይወት አምባው ደግሞ በ10 ኪሎ ሜትር ውድድር ሀገሯን ትወክላለች።

በተጨማሪም በድሬዳዋ እና አዲስ አበባ በተካሄዱ የወጣቶች ሻምፒዮናዎች አሸናፊ የሆነው አትሌት አብዱሰላም አብዱልወሀብ በወንዶች 10 ኪሎ ሜትር ለሜዳሊያ እንደሚፎካከር ታውቋል።

ይህ ለ31ኛ ጊዜ የሚካሄደው ሻምፒዮና የማራቶን ርምጃ እና የግማሽ ማራቶን ርምጃን ጨምሮ ከ20 ዓመት በታች የ10 ኪሎ ሜትር የርምጃ ውድድሮችን ያካተተ ሲሆን፤ ሁሉም የውድድር ዘርፎች በሁለቱም ጾታዎች (በወንዶችና በሴቶች) የሚከናወኑ ይሆናል። 

የልዑካን ቡድኑን በበላይነት በመምራት የፌዴሬሽኑ የፋሲሊቲ፣ ማህበራት እና አትሌቶች አገልግሎት ተወካይ ዳይሬክተር አቶ ተስፋዬ ይፍሩ የቴክኒክ ቡድን መሪ በመሆን አብረው ተጉዘዋል።

ቡድኑ በቦሌ ዓለም አቀፍ አየር ማረፊያ ሲሸኝ የተገኙት የፌዴሬሽኑ የሥራ አስፈፃሚ ኮሚቴ አባልና የኮሚኒኬሽን ንዑስ ኮሚቴ ሰብሳቢ አቶ ቢኒያም ምሩፅ፤ አትሌቶቹ በውድድሩ ጠንካራ ተፎካካሪ በመሆን የኢትዮጵያን ሰንደቅ ዓላማ ከፍ አድርገው እንዲያውለበልቡና በድል እንዲመለሱ መልካም ምኞታቸውን አስተላልፈዋል።

31ኛው የዓለም አትሌቲክስ የርምጃ ውድድር እሁድ ሚያዝያ 4 ቀን 2018 ዓ.ም በብራዚሊያ ይካሄዳል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም