ቀጥታ፡

ለትንሳኤ በዓል የሚሆኑ የፍጆታ ዕቃዎችና የእርድ እንስሳት በስፋት ቀርበዋል- ነጋዴዎችና ሸማቾች

አምቦ፤ ሚያዝያ 2/2018 (ኢዜአ)፦ በአምቦ ከተማ ለትንሳኤ በዓል የሚሆኑ የፍጆታ ዕቃዎች እና የእርድ እንስሳት በተሻለ ሁኔታ መቅረቡን ነጋዴዎችና ሸማቾች ገለጹ።

የከተማው ነዋሪ ወይዘሮ ትግስት ሽፈራው በከተማው ለበዓል ግብይት ተብሎ በተዘጋጀው ስፍራ ላይ ዘይት፣ ዱቄት እና ሌሎች ለበዓል ፍጆታ የሚውሉ ሸቀጦችን ይዘው መቅረባቸውን ገልጸዋል።   


 

በተለይም በከተማው ካለው መደበኛ ገበያ አንጻር የዘይትና የዱቄት ዋጋ ተመጣጣኝ መሆኑን ጠቅሰው፣ የበዓል ገበያውም የተረጋጋ ነው ብለዋል።   

ሌላው እንቁላል ለበዓል ገበያ ያቀረበው ወጣት አበራ አማና በበኩሉ፣ የገበያ ማዕከሉ ለነጋዴውም ሆነ ለሸማቹ ምቹ ሁኔታ መፍጠሩን ገልጾ፤ በቂ አቅርቦት በመኖሩ ሸማቹ እንደ ምርጫው እየገዛ መሆኑን ተናግሯል።


 

በከተማው የእርድ እንስሳት ገበያ ውስጥ ያገኘናቸው ሸማች አቶ ገዛኸኝ ሂርጵሳ እንደገለጹት፤ የበግና የፍየል አቅርቦት ከሌላው ጊዜ የተሻለ መሆኑን ገልጸዋል።   

ሆኖም ካለፈው ዓመት ጋር ሲነጻጸር መጠነኛ የዋጋ ጭማሪ መኖሩን ጠቅሰው በቂ አቅርቦት በመኖሩ በአማራጭ ለመገበያየት መቻላቸውን ተናግረዋል።   


 

ሌላዋ ሸማች ወይዘሮ ክብነሽ ሙሊሳ፤ የዶሮ አቅርቦት ጥሩ መሆኑን ገልጸው፤ በዓሉን ከቤተሰቦቻቸው ጋር ለማክበር መዘጋጀታቸውን ገልጸዋል።   


 

በአምቦ ከተማ አስተዳደር ንግድ ጽሕፈት ቤት የአትክልትና ፍራፍሬ ባለሙያ አቶ ደጀኔ ኢትሳ እንደገለጹት፤ በዓሉን ምክንያት በማድረግ ነጋዴዎች የፍጆታ ዕቃዎችን በበቂ ሁኔታ እንዲያቀርቡ የቅድመ ዝግጅት ሥራ ተከናውኗል።   


 

ህብረተሰቡ የኢንዱስትሪና የግብርና ምርቶችን በቀጥታ ከአምራቹ እንዲያገኝ በማድረግ የገበያ መረጋጋት ለመፍጠር ጥረት መደረጉን ገልጸዋል።   

በከተማው ዙሪያ የሚገኙ አርሶ አደሮችና ማህበራት ያደለቧቸውን እንስሳት ለገበያ እንዲያቀርቡ መደረጉን ጠቅሰው፤ በአሁኑ ወቅት የበሬ ዋጋ እንደ ደረጃው እየተሸጠ መሆኑ ተመልክቷል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም