በድሬደዋ ለትንሳኤ በዓል በቂ የእርድ እንሰሳት ለገበያ ቀርበዋል - ኢዜአ አማርኛ
በድሬደዋ ለትንሳኤ በዓል በቂ የእርድ እንሰሳት ለገበያ ቀርበዋል
ድሬደዋ፣ ሚያዝያ 2/2018(ኢዜአ)፡- በድሬደዋ ገበያዎች ለትንሳኤ በዓል በቂ የዕርድ እንሰሳትና ሌሎች የፍጆታ ቁሶች ለገበያ መቅረባቸውን ሸማቾች እና ነጋዴዎች ተናገሩ።
የኢዜአ ሪፖርተር በድሬደዋ ቀፊራን ጨምሮ በአሸዋ፣ በሰባተኛ፣ በሳብያንና በታይዋን አካባቢዎች የሚገኙ የገበያ ስፍራዎችን ቃኝቷል።
በገበያ ስፍራዎቹ ሲገበያዩ የነበሩ ሸማቾችና ነጋዴዎች እንደተናገሩት፤ ለትንሳኤ በዓል የበሬ፣ የፍየል፣ የዶሮ፣ የቅቤ፣ የቅመማቅመም ምርቶች በበቂ ደረጃ ቀርበዋል።
የበሬ ነጋዴው ወጣት መገርሳ ሁሴን እንዳለው በጥሩ መንገድ ያሳደጋቸውን የሐረር ሰንጋዎች ለገበያ አቅርቦ እስከ 200ሺህ ብር በመሸጥ ላይ ይገኛል።
ሰንጋዎቹ እንደ ገበያተኛው አቅም የቀረቡ እና መካከለኛዎቹን እስከ 120 ሺህ ብር ፣ አነስተኛዎቹን እስከ 80ሺህ ብር በመሸጥ ላይ መሆኑን ጠቅሶ የዘንድሮ ገበያ ከአምናው ተመሳሳይ ወቅት አንፃር በትላልቅ ሰንጋዎች ላይ ጭማሬ ታይቷል ብሏል።
አሸዋ ገበያ በሬ ሲያማርጡና በዋጋ ሲደራደሩ የነበሩት አቶ ግርማ ይመር ፤በተለያዩ የገበያ ቦታዎች በቂ ከብት ለገበያ መቅረቡን ተመልክተው ዘንድሮ በከብት በዋጋ ላይ መጠነኛ ጭማሬ መደረጉን ገልጸዋል።
ነገ የበለጠ ምርት ወደ ገበያ ስለሚገባ በተሻለ ዋጋ የተሻለ በሬ እንደሚያገኙ ጠቁመዋል።
የፍየል ሙክቶች በብዛት ለገበያ በሚቀርቡበት የአሸዋ ገበያ ለትንሳኤ በዓል በብዛት እና በዓይነት ማግኘት ይቻላል።
ፍየል ሲገዙ የነበሩት አቶ ፍሰሐ ዘገየ እንዳሉት፤ በዚህ የገበያ ስፍራ ሁሉም እንደ አቅሙ የፈለገውን ገዝቶ ወደ ቤቱ እየተመለሰ ነው።
በፍየሎች ዋጋ ላይ መጠነኛ ጭማሬ ቢስተዋልም እኔም አቅሜ የፈቀደውን መካከለኛ ፍየል ገዝቻለሁ ብለዋል።
የፍየል ነጋዴው ናስር አህመድ በበኩላቸው ለትንሳኤ በዓል በቂ አቅርቦት በገበያው በመመቻቸቱ የዘንድሮውን በዓል ልዩ ያደርገዋል ብለዋል።
በአሸዋ የፍየል ገበያ ከትልቅ ሙክት፣ እስከ አነስተኛ ፍየል ለገበያ መቅረባቸውን የኢዜአ ሪፖርተር አስተውሏል።
በድሬደዋ ትልቁ የቀፊራ ገበያ በብዛት በቀረቡት የዶሮ እና የእንቁላል ምርቶች ላይም መጠነኛ የዋጋ ጭማሪ መታየቱን እና የቅመማቅመም ምርቶች ግን በተለመደው ዋጋ ግብይት እየተካሄደ መሆኑን ወይዘሮ እታለም ታደሰ እና ወይዘሮ ቆንጅት ረታ ገልጸዋል።
ቀርሳ ተራ በተባለው የገበያ ስፍራ ዶሮዎችን ያቀረበችው ነጋዴ ወይዘሮ ጀነቲ አህመድ ትልቁን ዶሮ እስከ 1ሺህ 700 ትንሹን ደግሞ እስከ 1ሺህ ብር በመሸጥ ላይ መሆኗን አስታውሳለች።