ቀጥታ፡

የተጀመሩ የልማት ስራዎች ለስኬት እንዲበቁ ለማገዝና በምክክር ችግሮችን ለመፍታት የበኩላችንን እንወጣለን- የድሬዳዋ ነዋሪዎች

ድሬዳዋ፤ ሚያዚያ 2/2018 (ኢዜአ) ፡-የተጀመሩ የልማት ስራዎች ለስኬት እንዲበቁ ለማገዝና በምክክር ችግሮችን ለመፍታት የበኩላችንን እንወጣለን ሲሉ ኢዜአ ያነጋገራቸው የድሬዳዋ ነዋሪዎች ተናገሩ።

በለውጡ ዓመታት በድሬዳዋ የተከናወኑ ዘርፈ ብዙ የልማት ስራዎች ተጨባጭ ውጤቶች የተመዘገቡባቸው መሆኑን በብዙ መልኩ ማረጋገጥ ይቻላል።

በለውጡ የመጡ ስኬቶችን እውቅና ለመስጠትም የድሬዳዋ ህዝብ ወደ አደባባይ በመውጣት በድጋፍ ሰልፍ እውቅና መስጠት ችሏል።

የኢትዮጵያን ተስፋ እና የወደፊት እጣ ፋንታ የሚወስኑ ወሳኝ የልማት ስራዎች እየተከናወኑ መሆኑን አንስተው ከዳር እንዲደርሱ የሁላችንም ትብብር፣ ድጋፍና እገዛ ያስፈልጋል ሲሉ ተናግረዋል።

በመሆኑም በለውጡ የተጀመሩ የልማት ስራዎች ለስኬት እንዲበቁ ለማገዝና በምክክር ችግሮችን ለመፍታት የበኩላችንን እንወጣለን ሲሉ ኢዜአ ያነጋገራቸው የድሬዳዋ ነዋሪዎች ገልጸዋል።

ከአስተያየት ሰጪዎቹ መካከል የአፍረን ቀሎ አባገዳ አብዱረዛቅ አህመድ እና የሶማሌ ኢሳ ማህበረሰብ ባህላዊ መሪ ኡጋዝ ተወካይ ሐጂ አብዶ ኡመር፤ በኢትዮጵያ የቆዩ ችግሮች ያስከተሏቸው ስብራቶች እንዳሉ አንስተው በምክክር በዘላቂነት መፍታት ወሳኝ ስለመሆኑ ተናግረዋል።

ለዚህም ሀገራዊ የምክክር ሂደቱ ትልቅ ተስፋ የሰነቀ መሆኑን አንስተው ውጤታማ ሊሆን የሚችለው በችግሮቻችን ላይ መክረን ለመፍትሄው በጋራ መስራት ስንችል ነው ብለዋል።


 

ሌላኛው አስተያየት ሰጪ አቶ አክሊለ ታጠቅ እና አቶ አብዶ ሙሜ፤ በለውጡ የመጡ ስኬቶችን ዘላቂ ለማድረግ ህብረ ብሄራዊ ሀገራዊ አንድነትን ማጽናት ወሳኝ መሆኑን አንስተዋል።

በመሆኑም በሀገር ዋና ዋና ጉዳዮች ላይ የጋራ መግባባት መፍጠር የሚቻለው በችግሮቻችን ላይ መክረን የጋራ መፍትሄ መሻት ስንችል ነው ብለዋል።


 

ለዚህም ዜጎች ያለምንም ልዩነት ለሀገር ዘላቂ ሰላምና ለትውልድ ግንባታ አደራ ተቀብለን መስራት ስንችል ነው ሲሉ ተናግረዋል።

የኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን ለዘመናት እየተንከባለሉ የመጡ ሀገራዊ ችግሮችን በምክክር በመፍታት ለትውልዱ የምትመች ሀገር መገንባት ይቻላል በሚል መርህ እየሰራ መሆኑ ይታወቃል።

 

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም