የሲዳማ ቡና እና መቻል የሳምንቱ ተጠባቂ ጨዋታ - ኢዜአ አማርኛ
የሲዳማ ቡና እና መቻል የሳምንቱ ተጠባቂ ጨዋታ
አዲስ አበባ፤ ሚያዝያ 2/2018 (ኢዜአ)፦ የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ 26ኛ ሳምንት ዛሬ ይጠናቀቃል።
ከቀኑ 10 ሰዓት ላይ ሲዳማ ቡና ከመቻል በሃዋሳ ዩኒቨርሲቲ ስታዲየም የሚያደርጉት ጨዋታ የተመልካቾችን ትኩረት ስቧል።
ሲዳማ ቡና በሊጉ እስከ አሁን ባደረጋቸው 25 ጨዋታዎች 13ቱን ሲያሸንፍ፤ ሶስት ጊዜ ሽንፈት አስተናግዷል። በቀሪው ዘጠኝ ጨዋታዎች አቻ ተለያይቷል። በጨዋታዎቹ ላይ 31 ግቦችን ሲያስቆጥር 14 ግቦችን አስተናግዷል።
ሲዳማ ቡና በ48 ነጥብ አንደኛ ደረጃን ይዟል።
ተጋጣሚው መቻል በውድድር ዓመቱ ካደረጋቸው 23 ጨዋታዎች መካከል በዘጠኙ ድል ቀንቶታል። ስድስት ጊዜ ሲሸነፍ በ10 ጨዋታዎች አቻ ወጥቷል።
30 ግቦችን ከመረብ ጋር ሲያገናኝ 20 ግቦች ተቆጥረውበታል። መቻል በ37 ስድስተኛ ደረጃን ይዟል።
ሲዳማ ቡና ካሸነፈ የሊጉን መሪነት ያጠናክራል። ከተከታዩ ነገሌ አርሲ ጋር ያለውን የነጥብ ልዩነት ወደ ዘጠኝ ከፍ ያደርጋል።
ባለፉት ሶስት የሊጉ ጨዋታዎች አቻ የወጣው መቻል ወደ አሸናፊነት ለመመለስ ይጫወታል።
ጨዋታው ተመጣጣኝ ፉክክር ይታይበታል ተብሎ ይጠበቃል።
በሌላኛው መርሐ ግብር ባህር ዳር ከተማ ከአዳማ ከተማ ከቀኑ 9 ሰዓት በአበበ ቢቂላ ስታዲየም ይጫወታሉ።
ባሀር ዳር ከተማ በሊጉ ባደረጋቸው 25 ጨዋታዎች በስድስቱ ድል ሲቀናው፤ አምስት ጊዜ ተሸንፏል። በቀሪ 14 ጨዋታዎች አቻ ተለያይቷል። በጨዋታዎቹ ላይ 17 ግቦችን ሲያስቆጥር በተመሳሳይ 17 ግቦችን አስተናግዷል።
ቡድኑ በ32 ነጥብ 10ኛ ደረጃን ይዟል።
ተጋጣሚው አዳማ ከተማ በሊጉ እስከ አሁን 25 ጨዋታዎች አከናውኖ ሰባት ጊዜ ሲያሸንፍ፤ በስድስቱ ሽንፈት አስተናግዷል። በቀሪ 12 ጨዋታዎች ነጥብ ጥሏል። 23 ጎሎችን ከመረብ ላይ ሲያገናኝ 25 ግቦች ተቆጥረውበታል።
አዳማ ከተማ በ33 ነጥብ ዘጠነኛ ደረጃ ላይ ይገኛል።
በሊጉ በበርካታ ጨዋታዎች (14 ጊዜ) አቻ የወጣው ባህር ዳር ከተማ በ25ኛ ሳምንት ከኢትዮ ኤሌክትሪክ ጋር ካስመዘገበው የአቻ ውጤት በኋላ ወደ አሸናፊነት ለመመለስ ይጫወታል።
ባለፉት አምስት ጨዋታዎች ያላሸነፈው አዳማ ከተማ ሶስት ነጥብ ለማግኘት ይፋለማል።