ቀጥታ፡

ለበዓሉ ምርቶች በበቂ መጠንና በተመጣጣኝ ዋጋ ቀርበዋል-ሸማቾች

ጎንደር ፤ሚያዚያ 2/2018(ኢዜአ)፡- ለትንሳኤ በአል የሚያገለግሉ ምርቶች በበቂ መጠንና በተመጣጣኝ ዋጋ በመቅረባቸው አማራጭ ኖሮን ለመገበያየት አስችሎናል ሲሉ አስተያየታቸውን ለኢዜአ የሰጡ የጎንደር ከተማ ሸማቾች ገለጹ፡፡

በከተማው በ6 ክፍለ ከተሞች በተቋቋሙ የድንኳን ጊዜያዊ ገበያዎች የግብርናና የኢንዱስትሪ ምርቶች በብዛት፣ በዓይነትና በተመጣጣኝ ዋጋ ለህብረተሰቡ ማቅረብ ተችሏል።


 

የከተማዋ ሸማቾች እንደገለጹት፤ለትንሳኤ በአል የሚያገለግሉ ምርቶች በበቂ መጠንና በተመጣጣኝ ዋጋ በመቅረባቸው አማራጭ ኖሮን ለመገበያየት አስችሎናል።

የከተማዋ ነዋሪ የሆኑት ወይዘሮ አድና ጠጋው ለኢዜአ እንደገለጹት በመደበኛ ገበያው 70 ብር የሚሸጠውን አንድ ኪሎ ሽንኩርት በጊዜያዊ ገበያው በ45 ብር በመግዛት ተጠቃሚ መሆናቸውን ተናግረዋል። 

መንግስት በበዓል ወቅት አማራጭ የገበያ እድሎችን ማመቻቸቱ የገቢ መጠናቸው አነስተኛ ለሆኑ የህብረተሰብ ክፍሎች እንደ አቅማቸው በመገበያየት በዓሉን በደስታ እንዲያሳልፉ ያስችላል ብለዋል።

ሌላዋ የከተማዋ ነዋሪ ወይዘሪት ክብካብ አለማየሁ በበኩሏ በዓሉን ምክንያት በማድረግ በሸማቾች መሰረታዊ ማህበራት በኩል የቀረቡ የፍጆታ ምርቶች ሸማቹ ማህበረሰብ ተረጋግቶ እንዲሸምት ምቹ የገበያ እድል የፈጠረ ነው ብላለች፡፡

እርሷም ለበዓሉ ዘይት፣ ዱቄትና ስኳርን ከመደበኛ ገበያው ቅናሽ በሆነ ዋጋ መግዛቷን ጠቁማ በጊዜያዊ ገበያው ሌሎች ምርቶችም በተመጣጣኝ ዋጋ መቅረባቸውን ተናግራለች። 

የዘንድሮ የበዓል ገበያ በቂ የፍጆታ ምርት ወደ ገበያ የገባበትና በዋጋ ደረጃም ቢሆን በተወሰደው የገበያ ማረጋጋት ስራ የሸማቹን ኪስ የማይጎዳ ነው ያለው ደግሞ ወጣት አበበ ዳገት ነው፡፡

የጎንደር ከተማ የራስ ዳሽን ሸማቾች ህብረት ስራ ዩኒየን ስራ አስኪያጅ ወይዘሮ አድና አለምዬ ዩኒየኑ በ25 ሚሊዮን ብር ወጪ የግብርናና የኢንዱስትሪ ምርቶችን በማስገባት በተመጣጣኝ ዋጋ ለህብረተሰቡ አቅርቧል ብለዋል።

በዚህም ሁሉንም ምርቶች ከሌላው የገበያ ዋጋ እስከ 20 በመቶ በመቀነስ ሁለት ሺ ኩንታል ጤፍ፣ 100 ኩንታል ስኳር፣ የምግብ ዘይትና ፓስታ ለሽያጭ ማቅረቡን አብራርተዋል፡፡

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም