ቀጥታ፡

የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች በሰባተኛው ጠቅላላ ምርጫ የሚኖራቸውን የክትትልና ድጋፍ ሚና አጠናክረው ሊቀጥሉ ይገባል

አዲስ አበባ፤ ሚያዝያ 1/2018 (ኢዜአ)፡-የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች በሰባተኛው ጠቅላላ ምርጫ የሚኖራቸውን የክትትልና ድጋፍ ሚና አጠናክረው ሊቀጥሉ እንደሚገባ በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የሕግና ፍትሕ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ አሳሳበ። 

በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የሕግና ፍትሕ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ የሲቪል ማሕበረሰብ ድርጅቶች ባለሥልጣን የ2018 ዓ.ም በጀት ዓመት የዘጠኝ ወራት የዕቅድ አፈጻጸም ሪፖርት ገምግሟል።


 

በዚሁ ጊዜ የቋሚ ኮሚቴው ሰብሳቢ እጸገነት መንግስቱ፤ በሰባተኛው ጠቅላላ ምርጫ ላይ የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች ከፍተኛ አስተዋጽኦ እያበረከቱ ይገኛል ብለዋል።

ባለሥልጣኑም የሲቪል ማህበረሰብ የድርጅቶች ምዝገባና ቁጥጥር፣ ለሀገር ልማትና ዴሞክራሲ ሥርዓት ግንባታ የሚያበረክቱትን አስተዋፅኦ ማጠናከር እንደሚጠበቅባቸው አሳስበዋል።

በኢትዮጵያ ሰባተኛው ጠቅላላ ምርጫ ነጻ፣ ፍትሕዊና ዴሞክራሲያዊነትም የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች ድጋፍና ክትትል ተጠናክሮ ሊቀጥል እንደሚገባ አስገንዝበዋል።

የሕግና ፍትሕ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ አባላትም፤ ባለስልጣኑ በሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች ምዝገባና ክትትል የዲጂታላይዜሽን ሥርዓት ለማዘመን የተከናወኑ ተግባራትን ጠይቀዋል። 

በተጨማሪም በሰባተኛው ጠቅላላ ምርጫና በሀገር የልማትና ዴሞክራሲ ባህል ግንባታ የበጎ ፈቃድ ሥራዎች ጋር የተያያዙ አስተያየትና ጥያቄዎችን አቅርበዋል።

የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች ባለስልጣን ምክትል ዋና ዳይሬክተር ፋሲካው ሞላ፤ ሀገራዊ ለውጡ የፈጠረው ተቋማዊ የለውጥ እርምጃ ለሰቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች እንቅስቃሴ አስቻይ ሁኔታን ፈጥሯል ብለዋል።

የባለስልጣኑ አገልግሎቶችን  ሙሉ ለሙሉ ዲጂታላይዝ ለማድረግ መታቀዱን አመልክተው፤ የተወሰኑ አገልግሎቶችን ወደ መሶብ የአንድ ማዕከል አገልግሎት ለማስገባት ዝግጅት እየተደረገ ነው ብለዋል።

የበጎ አድራጎት ስራዎችን ለማሳደግ ‘ቅን ልብ’ የተሰኘ መተግበሪያ ተግባራዊ መደረጉን ተናግረዋል።

የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች ላይ የሚደረገውን ክትትል ለማጠናከር ውጤታማና ስጋትን መሰረት ያደረገ የመሰክ ምልከታ እየተደረገ መሆኑን ጠቁመው፤ ከክልሎች ሲቪል ማህበረሰብ ደርጅቶች ምክር ቤቶች ጋር በጋራ እየተሰራ ነው ብለዋል።

በሰባተኛው ጠቅላላ ምርጫ የድርጅቶቹን ሚና ለማጎልበት  እየተከናወኑ የሚገኙ ስራዎችንም አብራርተዋል። 

የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች ባለስልጣን ዋና ዳይሬክተር አቶ ሳምሶን ቢራቱ በበኩላቸው፤ ከምዝገባ ጀምሮ ወደ ስራ የተሰማሩ የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች ላይ የሚደረገው ክትትል ለማጠናከር የተሰሩ ስራዎቸን አብራርተዋል። 

የምክር ቤቱ የህግና ፍትህ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ሰብሳቢ እጸገነት መንግስቱ፤ የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች በምርጫው  ሂደት ገለልተኛና  ነጻ ሆነው በስፋት እንዲሰሩ የሚደረገው  ክትትል ማጠናከር ያሰፈልጋል ብለዋል።

ባለስልጣኑ በዲጂታላይዜሽንና በሰው ሀይል አቅም ግንባታ፣ የበጎ ፍቃደኝነት ስራዎችን ለማጎልበትና የምዝገባና ሂደቱን በጥንቃቄ ለማካሄድ  እየተከናወኑ የሚገኙ ስራዎች የሚበረታቱ መሆናቸውን አንስተዋል።   

ድርጅቶቹ በተቋቋሙበት ዓላማ መሰረት እየሰሩ መሆናቸውን እንዲሁም ጠንካራ አገሪቷን የሚመጥኑ ድርጅቶችን ለማስፋፋት መስራት ይገባል ብለዋል።

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም