ቀጥታ፡

ኢትዮጵያ ከብሔራዊ ልማት አጀንዳ ጋር የተቀናጀ አደጋን የመቋቋም አቅም እየገነባች ነው-ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ተመስገን ጥሩነህ

አዲስ አበባ፤ ሚያዝያ 1/2018 (ኢዜአ)፡-ኢትዮጵያ ከብሔራዊ ልማት አጀንዳ ጋር የተቀናጀ አደጋን በራስ የመቋቋም አቅም በመገንባት ረገድ ለአፍሪካ የተግባር ምሳሌ መሆኗን ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ተመስገን ጥሩነህ ገለጹ።

16ኛው የአፍሪካ አደጋ ስጋት አቅም ጉባኤ ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ተመስገን ጥሩነህ፣ የአፍሪካ ህብረት ኮሚሽን ምክትል ሊቀመንበር ሳልማ ማሊካ ሃዳዲና ሌሎች የጉባኤው ተሳታፊዎች በተገኙበት በአዲስ አበባ ተካሂዷል።


 

ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ተመስገን ጥሩነህ በጉባኤው ባደረጉት ንግግር የአየር ንብረት ለውጥ ጉዳት ቢጨምርም ዓለም አቀፋዊ ትብብርና መደጋገፍ እየላላ መጥቷል ብለዋል።

በኢኮኖሚ እና የፖለቲካ ለውጦች ለሰብዓዊ ምላሽ የሚውል የድጋፍ ሀብት መቀነሱን አንስተዋል።

ኢትዮጵያ የአየር ንብረት ለውጥ የሚያስከትለውን አደጋ ጠንቅቃ  ከመገንዘብ ባለፈ የጉዳቱ ገፈት ቀማሽ በመሆኗ የመቋቋም አቅምን የሚያጠክሩ እርምጃዎችን መውሰድ መጀመሯን ገልጸዋል።

የረጅም ጊዜ ዝቅተኛ የካርቦን ልቀት እና የአየር ንብረት መቋቋም ልማት ስትራቴጂን በመቅረጽ ለሀገራዊ እድገት እና ለዓለም አቀፋዊ ምላሽ ያላትን ቁርጠኝነት ማሳየቷን ጠቅሰዋል።

ሀገር በቀል ፖሊሲዎችን በሁሉም መስኮች በውጤታማነት እየተገበረች ነው ያሉት ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትሩ፥ከብሔራዊ  የልማት አጀንዳዎች ጋር የተቀናጀ የአደጋ መቋቋም አቅም እየገነባች ነው ብለዋል።

የአረንጓዴ አሻራ፣ የምግብ ሉዓላዊነት፣ የኮሪደር ልማት፣ የታዳሽ ኃይል እና የሰብዓዊ ድጋፍ ሉዓላዊነት አደጋን በራስ አቅም የመቋቋምና በፈተና የማትበገር ሀገር የመገንባት ወሳኝ አምዶች መሆናቸውንም አስረድተዋል።

ዘላቂ መጻኢ እድልን ለማረጋገጥ ትልቅ አቅም እንደሚፈጥሩ በማንሳት፥ ከኢትዮጵያ አልፎ ፋይዳና ተሞክሮነታቸው ለአፍሪካ እንደሚተርፍ ገልጸዋል።

ከዚህ አኳያ የአፍሪካ አደጋ ስጋት አቅም አህጉሪቱ በሳይንስና በፈጠራ በመታገዝ በጋራ የመስራትና ችግሮችን የመቋቋም አቅምን የሚያሳይ  ነው ብለዋል።

ተቋሙ አፍሪካውያን ከአደጋ በኋላ ምላሽ ከመስጠት ይልቅ ለአደጋ ቀድሞ ወደ መዘጋጀት እንዲሸጋገሩ እያገዘ መሆኑን  ጠቅሰው፥ በአጀንዳ 2063 ራሷን የቻለች፣ የማትበገርና የተባበረች አፍሪካን ለመገንባት ትልቅ አቅም መሆኑን ጠቅሰዋል።

የመቋቋም አቅምን ለመገንባት በሀገራት፣ በተቋማት እና በዘርፎች መካከል ያለውን ትብብር፣ መተማመን፣ መደጋገፍና የጋራ አመራርን ማጠናከር እንደሚገባ አንስተዋል።

ለዚህ ደግሞ አፍሪካ ግዙፍ አቅም፣ ሀብት፣ እውቀት እንዳላት ገልጸው፥  የሚያስፈልገን በአንድነት እና በዓላማ መነሳት ብቻ ነው ብለዋል።

ከአደጋ ስጋት ወደ አይበገሬነት የሚደረገው ጉዞ ራዕይን፣ ቁርጠኝነትን እና ቀጣይነት ያለው እርምጃን እንደሚጠይቅም አንስተዋል።

የአፍሪካ አደጋ ስጋት አቅም የአፍሪካ የአንድነትና የሉዓላዊነት ምሰሶ በመሆኑ የያዘው ግብ እንዲሳካ የፖለቲካ ቁርጠኝነት፣ ዘላቂ ፋይናንስ እና ጠንካራ ቴክኒካዊ አቅም እንደሚያስፈልግ ገልጸዋል።

 

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም