ሰባተኛውን ጠቅላላ ምርጫ ነጻና ሰላማዊ ለማድረግ የሚያግዝ አስቻይ የደኅንነት ዝግጅት ተደርጓል - ኢዜአ አማርኛ
ሰባተኛውን ጠቅላላ ምርጫ ነጻና ሰላማዊ ለማድረግ የሚያግዝ አስቻይ የደኅንነት ዝግጅት ተደርጓል
አዲስ አበባ፤ ሚያዝያ 1/2018(ኢዜአ) ፦በዘንድሮው ጠቅላላ ምርጫ የኢትዮጵያን ብሔራዊ ጥቅም የሚያስጠብቅ ጠንካራ መንግሥት መመስረት የሚያግዝ አስቻይ የደኅንነት ዝግጅት መደረጉን የብሔራዊ መረጃና ደኅንነት አገልግሎት ምክትል ዳይሬክተር ጀነራሎች ገለጹ፡፡
በብሔራዊ መረጃና ደኅንነት አገልግሎት የብሔራዊ ደኅንነት ዩኒቨርሲቲ የምርጫ ደኅንነት ስልጠና ማጠናቀቂያ መርሃ ግብር አካሂዷል።
በዚሁ ወቅት የብሔራዊ መረጃና ደኅንነት አገልግሎት ምክትል ዳይሬክተር ጀነራል ሲሳይ ቶላ፤ በሰባተኛው ጠቅላላ ምርጫ የህዝባችንን የስልጣን ባለቤትነት የሚያረጋግጥ አስቻይ የደኅንነት ዝግጅት አስፈላጊ ነው ብለዋል።
ዜጎች ሰላማዊና ነፃ ምርጫ በማድረግ ጠንካራ መንግሥት መመስረት የሚያስችላቸውን ምቹ ሁኔታ ለመፍጠር የደኅንነትና ፀጥታ ተቋማት በቂ ዝግጅት ማድረጋቸውንም ገልጸዋል።
ምክትል ዳይሬክተር ጀነራሉ እንደገለጹት፤ እያንዳንዱ ምርጫ በየአምስት ዓመቱ ከሚደረግ ሁነት ባሻገር ለኢትዮጵያ ብሔራዊ ጥቅም የሚያመጣው ወሳኝ ነገር አለ።
ለዚህም በሀገር አቀፍ ደረጃ ሁሉንም የፀጥታና ደኅንነት ተቋማት የያዘ ዕቅድ በማውጣት ካለፉት ስምንት ወራት ጀምሮ ሰፋፊ ተግባራትን በማከናወን ወደ ተግባር መገባቱን አስረድተዋል።
በሀገራዊ ለውጡ ማግስት የተካሄደው ስድስተኛው ሀገራዊ ምርጫም የፀጥታና ሌሎች ፈታኝ ጉዳዮችን በማለፍ ሉዓላዊ አንድነትን የሚያስቀጥል መንግሥት ለመመስረት ያስቻለ እንደነበር አስታውሰዋል።
የዘንድሮው ምርጫም ኢትዮጵያ ባለፈችባቸው ወሳኝ ምዕራፎች ውስጥ በዜጎች ይሁንታ የተመሰረተ ጠንካራ መንግሥት ለመመስረት ትርጉም የሚሰጠው መሆኑን አስገንዝበዋል።
ከኢትዮጵያ ህልውና ጋር የተቆራኙትን የዓባይ ተጠቃሚነትን በታላቁ ሕዳሴ ግድብ እውን መሆኑን ጠቁመው፤ የቀይ ባሕር ተጠቃሚነቷን ለማረጋገጥም ፍትሕዊና ሕጋዊ ጥያቄ እያቀረበች መሆኗን አንስተዋል።
ለዚህም የኢትዮጵያን ሀገራዊ፣ ቀጣናዊና ዓለም አቀፋዊ ብሔራዊ ጥቅም ለማስከበር በህዝብ ይሁንታ ጠንካራ መንግሥት መመስረት የሚያስችል አስቻይ የምርጫ ዝግጅት ተደርጓል ብለዋል።
የብሔራዊ ደኅንነት ዩኒቨርሲቲ በሁሉም የሀገሪቷ አካባቢዎች በቴክኖሎጂና በበጎ ሥነ-ምግባር የተካኑ ሙያተኞች ሰልጥነው ስምሪት መውሰዳቸውን አስረድተዋል።
የኢትዮጵያን ብሔራዊ ጥቅም የሚያስቀድም ሰላማዊና ፍትሕዊ ምርጫ ለማካሄድ በሙያዊ ክህሎትና ሥነ-ምግባር ቴክኖሎጂን የሚጠቀም ሙያተኛ ስምሪት መሰጠቱን አስታውቀዋል።
የምርጫ ሰላማዊነትን ለማስጠበቅም የድሮን፣ የፀረ-ድሮንና የኮሙዩኒኬሽን ቴክኖሎጂ በመጠቀም መረጃን በመሰብሰብና በመተንተን ለውሳኔ ሰጪ አካል በፍጥነት ማቅረብ የሚያስችል የላቀ ዝግጅት መደረጉን አረጋግጠዋል።
የብሔራዊ መረጃና ደኅንነት አገልግሎት ምክትል ዳይሬክተር ጀነራል አሰፋ አብዩ (ዶ/ር)፤ ሰባተኛው ጠቅላላ ምርጫ ነጻ፣ ሰላማዊ፣ ተዓማኒ፣ ፍትሕዊና ዴሞክራሲያዊነት የሚያስጠብቅ የደኅንነት ዝግጅት ተደርጓል ብለዋል።
ለዚህም በምርጫው ሂደት ሊከሰቱ የሚችሉ የደኅንነት ስጋቶችን በመዳሰስ ሀገራዊ፣ ቀጣናዊና ዓለም አቀፋዊ ሁኔታን በማጥናት ሰፊ ዝግጅት መደረጉን አስረድተዋል።
ከፌዴራል እስከ ታችኛው ድረስ ባሉ መዋቅሮች በጥናት የተጠናቀሩና የሚጠናቀሩ መረጃዎችንም በመሰብሰብ፣ በመተንተንና ለውሳኔ ሰጪ አካል በማቅረብ ጥቅም ላይ እንዲውል እየተሰራ መሆኑን ተናግረዋል።
የምርጫ ሂደቱን የደኅንነት ሁኔታ ለማስጠበቅም የብሔራዊ ደኅንነት ዩኒቨርሲቲ ለአገልግሎቱ ሙያተኞች ወሳኝ ስልጠና በመስጠት አቅም እየገነባ እንደሚገኝ አንስተዋል።
በዩኒቨርሲቲው የሚሰጠው ስልጠናም ከምርጫ ባሻገር የኢትዮጵያን ብሔራዊ ጥቅምና ፍላጎት የሚያስጠበቅ የመረጃ ኦፊሰሮችን በማፍራት ከፍተኛ አስተዋጽኦ እያበረከተ መሆኑን አንስተዋል።
የብሔራዊ ደኅንነት ዩኒቨርሲቲ ፕሬዚዳንት በበኩላቸው፤ የኢትዮጵያን ብሔራዊ ጥቅምና ደኅንነት ማሳደግ፣ መጠበቅና መከላከል የሚያስችል ጠንካራ የመረጃ ኪነ-ሙያና በዕውቀትና ክህሎት የተካነ የሰው ሃብት መገንባት ያስፈልጋል ብለዋል፡፡
ለዚህም ወቅታዊና አሁናዊ ቀጣናዊና ዓለም አቀፋዊ ተለዋዋጭ አሰላለፎችን፣ ስጋትና መልካም አጋጣሚዎችን በተገቢው መንገድ በመተንተን ምላሽ የሚሰጥ ብቁ የሰው ሃይል መገንባት የሚያስችል ስልጠና እየተሰጠ መሆኑን ገልጸዋል።
በምርጫ ደኅንነት የተሰጠው ስልጠናም የዚሁ ተግባር አንዱ ማሳያ መሆኑን ጠቅሰዋል።