ቀጥታ፡

የክፍያ ስርዓቱ የትራንስፖርት ዘርፍ አገልግሎቱን በማዘመን የኢኮኖሚ እንቅስቃሴን ለማሳለጥ ምቹ ሁኔታን የሚፈጥር ነው

አዲስ አበባ፤ ሚያዝያ 1/2018 (ኢዜአ)፡- ኢትዮ-ቴሌኮም ያስጀመረው የክፍያ ስርዓት የትራንስፖርት ዘርፍ አገልግሎትን በማዘመን የሀገርን የኢኮኖሚ እንቅስቃሴ ለማሳለጥ ምቹ ሁኔታን የሚፈጥር መሆኑ ተገለጸ።

ኢትዮ-ቴሌኮም "ቶሎ" የተሰኘ ዲጂታል የክፍያ ስርዓት ዛሬ አስጀምሯል።


 

የዲጂታል ክፍያ ስርዓቱ የኢትዮ ቴሌኮም ዋና ስራ አስፈፃሚ ፍሬህይወት ታምሩ እና የኢትዮጵያ ክፍያ መንገዶች ኢንተርፕራይዝ ዋና ስራ አስፈፃሚ ሙስጠፋ አባሲመል በቱሉ ዲምቱ ዋና የክፍያ ጣቢያ አስጀምረዋል።

የኢትዮ-ቴሌኮም ዋና ሥራ አስፈጻሚ ፍሬህይወት ታምሩ በዚህ ወቅት እንደተናገሩት፤ ተቋሙ ዲጂታል ኢትዮጵያን እውን ለማድረግ የሚያስችሉ የተለያዩ አገልግሎቶችን ተግባራዊ እያደረገ ይገኛል።

ኢትዮ-ቴሌኮም ከመደበኛ የቴሌኮም አገልግሎት ባሻገር ቀልጣፋ፣ ምቹና ወጪ ቆጣቢ አገልግሎት በማቅረብ የፋይናንስ ዘርፉን እየደገፈ መሆኑንም አስረድተዋል።

በዚህም የሀገርን ልማት ዘላቂና አካታች ለማድረግ የዲጂታል መሰረተ ልማት ዝርጋታ ላይ ትኩረት በማድረግ በርካታ ተግባራት ማከናወኑን ገልጸዋል።

ኢንተርፕራይዙ በቀን ከ32 ሺህ በላይ ተሽከርካሪዎችን የሚያስተናግድ እንደመሆኑ፣ አዲሱ የ"ቶሎ" ዲጂታል ክፍያ አሠራር ጊዜን ከመቆጠብ ባሻገር የአገልግሎት ጥራትንና የመንገድ ደኅንነት ቁጥጥርን ማረጋገጥ የሚያስችል ነው።

በኢትዮጵያ ኢንቨስትመንት ሆልዲንግ ሥር የሚገኘው ይህ ተቋም፣ አገልግሎቱን 100 በመቶ ዲጂታል ለማድረግና አረንጓዴ ኢነርጂን ተግባራዊ ለማድረግ እየሠራ እንደሚገኝም ተመላክቷል።

ዛሬ የተጀመረው የዲጂታል ክፍያ መርሃ ግብርም የትራንስፖርት ዘርፉን አገልግሎት በማሳለጥ የሀገርን የኢኮኖሚ እንቅስቃሴ ለማሳደግ ምቹ ሁኔታን የሚፈጥር ነው ብለዋል።

ይህም ደንበኞች ለዚሁ ዓላማ የተዘጋጀ ካርድ ተጠቅመው ክፍያ እንዲፈጽሙ የሚያስችል መሆኑ ገልጸዋል።


 

የኢትዮጵያ የክፍያ መንገዶች ኢንተርፕራይዝ ዋና ስራ አስፈፃሚ ሙስጠፋ አባሲመል በበኩላቸው፤ ካሁን ቀደም ወረቀት መሰረት ያደረገ ክፍያ ስርዓት ይከናወን እንደነበረ ገልፀዋል።

ዲጂታል ኢትዮጵያን እውን ለማድረግ አገልግሎት አሰጣጡን በቴክኖሎጂ ማስደገፍ አስፈላጊ መሆኑን አመልክተው፤ አገልግሎቱ ሙሉ ለሙሉ ዲጂታላይዝ የማድረግ ጉዞ ዛሬ መጀመሩን ይፋ አድርገዋል።

"ቶሎ" የተሰኘ የክፍያ ስርዓት ሶፍትዌር መልማቱን አመልክተው፤ ይህም ከኢትዮ ቴሌኮም ጋር በመተባበር ከቴሌ ብር ጋር በማስተሳሰር ዘመናዊ የክፍያ ስርዓት መጀመሩ አብስረዋል።

በዚህም ደንበኞች የተዘጋጀውን ካርድ በመጠቀም ክፍያ እንዲፈፅሙ በማስቻል ፈጣንና ቀልጣፋ አገልግሎት እንደሚያገኙ ተናግረዋል።

የክፍያ ስርዓቱ የመንግሥት አገልግሎቶችን በማዘመን ግልጽና የአሰራር ቅልጥፍና የሰፈነበት የዲጂታል ኢኮኖሚ ለመገንባት ያለውን ቁርጠኝነት በተግባር የሚያሳይ ነው ብለዋል።

ሁለቱ ተቋማት በቀጣይ አብሮ መስራት የሚያስችል የስምምነት ፊርማ ስነ-ስርዓት አካሂደዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም