ቀጥታ፡

የአረንጓዴ አሻራ መርሃ ግብር የፖለቲካ ቁርጠኝነትና የሕብረተሰብ ንቁ ተሳትፎ የታየበት በአፍሪካ ቀዳሚ ኢንሼቲቭ ነው

አዲስ አበባ፤ ሚያዝያ 1/2018 (ኢዜአ)፡-የአረንጓዴ አሻራ መርሃ ግብር የፖለቲካ ቁርጠኝነትና የህብረተሰብ ንቁ ተሳትፎ የታየበት በአፍሪካ ቀዳሚ ኢንሼቲቭ መሆኑን የብሄራዊ አረንጓዴ አሻራ የቴክኒክ ኮሚቴ ሰብሳቢ አደፍርስ ወርቁ (ዶ/ር) ገለጹ።

ኢትዮጵያ የምታስተናግደው 16ኛው የአፍሪካ አደጋ ሥጋት አቅም አህጉራዊ ጉባኤ "ለሉዓላዊነት መተባበር" በሚል መሪ ሀሳብ በአዲስ አበባ የአፍሪካ ኢኮኖሚ ኮሚሽን እየተካሄደ ነው።


 

የአፍሪካ አደጋ ሥጋት አቅም አባል ሀገራትና ታዛቢዎች እንዲሁም የዘርፉ ተዋንያን የሚሳተፉበት ጉባኤው በአፍሪካውያን መካከል ትብብርና አጋርነትን በመፍጠር አህጉራዊ የአደጋ ሥጋትን የመከላከልና የፋይናንስ አቅምን ማጠናከርን ያለመ ነው።

ጉባኤው የአየር ንብረት ለውጥ ተፅዕኖን ለመቋቋም፣ ለአደጋ ስጋት ምላሽ ለመስጠት እና የምግብ ሉዓላዊነትን ለማረጋገጥ አፍሪካ መር መፍትሔ ማፈላለግ በሚያስችሉ ጉዳዮች ላይ ምክክርና የጋራ መግባባት መፍጠር ያስችላል።

የብሄራዊ አረንጓዴ አሻራ የቴክኒክ ኮሚቴ ሰብሳቢ አደፍርስ ወርቁ (ዶ/ር) በመድረኩ ኢትዮጵያ በአረንጓዴ አሻራ መርሃ ግብር ያስመዘገበችውን ስኬትና ለአፍሪካ ያላትን ተሞክሮ አቅርበዋል።

ኢትዮጵያ በአረንጓዴ አሻራ መርሃ ግብር የመጀመሪያ ምዕራፍ 50 ቢሊዮን ችግኞችን ለመትከል ስታቅድ በወቅቱ ምሁራን ሳይቀሩ ዕቅዱ ሊሳካ አይችልም የሚል ጥርጣሬ እንደነበራቸው አስታውሰዋል።

የአረንጓዴ አሻራ መርሃ ግብር የጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) እሳቤ መሆኑን ጠቅሰው፤ የተራቆተ መሬትን እንዲያገግም ማድረግ ሥነ-ምህዳሩን መመለስ እና ለግብርናና ከተማ ልማት ምቹ ከባቢ መፍጠር ነው ብለዋል።

በዚህም የተለያዩ ሀገር በቀል እና ለተለያዩ አገልግሎት የሚውሉ ችግኞችን በመትከል የኢትዮጵያን ምድር አረንጓዴ ማልበስ መጀመሩን ገልጸዋል።

የአረንጓዴ አሻራ መርሃ ግብር ከቀጣይነት ያለው የተፈጥሮ ሃብት ጥበቃን በማጠናከር የግብርና ሥራዎች ምቹ ሥነ-ምህዳር መፍጠሩን ተናግረዋል። 

የአረንጓዴ አሻራ የመላው ኢትዮጵያውያንና ተቋማት ትብብር የጋራ ውጤት ነው ብለዋል።

የአረንጓዴ አሻራ ከጠቅላይ ማኒስትሩ ጀምሮ የሁሉም አመራር ቁርጠኝነት የታየበት መሆኑን ጠቅሰው፤ ለጎረቤት ሀገራት ጭምር ተሞክሮ ሆኗል ብለዋል።

የኢትዮጵያ የአረንጓዴ አሻራ መርሃ ግብር በሌሎች የአፍሪካ ሀገራት ጭምር ተቀባይነት ማግኘቱን ገልፀው፣ ኬንያ በአስር ዓመት ውስጥ 15 ቢሊየን ችግኝ ለመትከል ተሞክሮ መውሰዷን ተናግረዋል።

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም