ቀጥታ፡

የአፍሪካን ችግሮች በአፍሪካ የፋይናንስ ተቋማት ለመፍታት ሀገራት ትብብራቸውን ሊያጠናክሩ ይገባል

አዲስ አበባ፤ ሚያዝያ 1/2018 (ኢዜአ)፡- የአፍሪካን ችግሮች በአፍሪካ የፋይናንስ ተቋማት በመፍታት ከውጭ ጥገኝነት ለማውጣት ሀገራት ትብብራቸውን ማጠናከር እንዳለባቸው የአፍሪካ ሕብረት ኮሚሽን ምክትል ሊቀ መንበር አምባሳደር ሰልማ ማሊክ ሀዳዲ ገለጹ።

ኢትዮጵያ የምታስተናግደው16ኛው የአፍሪካ አደጋ ሥጋት አቅም አህጉራዊ ጉባኤ "ለሉዓላዊነት መተባበር" በሚል መሪ ሀሳብ በአዲስ አበባ የአፍሪካ ኢኮኖሚ ኮሚሽን እየተካሄደ ነው።


 

የአፍሪካ አደጋ ሥጋት አቅም አባል ሀገራትና ታዛቢዎች እንዲሁም የዘርፉ ተዋንያን የሚሳተፉበት ጉባኤው በአፍሪካውያን መካከል ትብብርና አጋርነትን በመፍጠር አህጉራዊ የአደጋ ሥጋትን የመከላከልና የፋይናንስ አቅምን ማጠናከርን ያለመ ነው።

ጉባኤው የአየር ንብረት ለውጥ ተፅዕኖን ለመቋቋም፣ ለአደጋ ስጋት ምላሽ ለመስጠት እና የምግብ ሉዓላዊነትን ለማረጋገጥ አፍሪካ መር መፍትሔ ማፈላለግ በሚያስችሉ ጉዳዮች ላይ ምክክርና የጋራ መግባባት መፍጠር ያስችላል።

የአፍሪካ ህብረት ኮሚሽን ምክትል ሊቀ-መንበር አምባሳደር ሰልማ ማሊክ ሀዳዲ በዚህ ወቅት እንዳሉት፤ የአፍሪካ ሕብረት አባል ሀገራት እንደ አፍሪካ አደጋ ስጋት አቅም ያሉ ተቋማት ጋር በጋራ መስራት አለባቸው።

በአፍሪካ የአየር ንብረት ለውጥ የሚያመጣው ማህበራዊ፣ ኢኮናሚያዊና የስነ-ምህዳር ለውጥ ጊዜ የሚሰጠው አይደለም ብለዋል።

አፍሪካ ለአየር ንብረት ለውጥ ተፅዕኖ ያላት ድርሻ ከአራት በመቶ በታች ቢሆንም አምስት በመቶ ጥቅል አህጉራዊ ሀብቷን እያሳጣት መሆኑን ገልጸዋል።

አሕጉራዊ ችግሮች አህጉራዊ መፍትሔ እንደሚሹ ገልጸው፤ የአፍሪካ የፋይናንስ ተቋማት ለአፍሪካ ችግሮች ቅድሚያ መስጠት አለባቸው ብለዋል።

አሕጉራዊ ማዕቀፎችና ፖሊሲዎች ከዚህ ጋር መጣጣም እንዳለባቸው ጠቅሰው፤ ችግሩን በዘላቂነት በራስ አቅም ለመፍታት በቴክኖሎጂ የታገዘ ቀጣይነት ያለው የፋይናንስ ስርዓት መዘርጋት ይገባል ብለዋል።

የአየር ንብረት ለውጥ ተፅዕኖን ለመቋቋም በአፍሪካ ሕብረት አባል ሀገራት መካከል ያለው ትብብር በማሳደግ የፋይናንስ አቅም ማጠናከር እንደሚገባ ገልጸዋል።

ከተናጠል እርምጃ ይልቅ በአባል ሀገራት መካከል ትብብርን ማጠናከርና ወደ ተግባር መቀየር ይገባል ያሉት ምክትል ሊቀ መንበሯ፤ አህጉራዊ የትኩረት መስኮች ላይ መተባበር ወሳኝ መሆኑን ገልጸዋል።

አፍሪካ ከውጭ በሚመጣ ፋይናንስ ጥገኛ መሆን እንደሌለባት ጠቅሰው፤ ለአፍሪካ መፍትሔ ሀገር በቀል ዕውቀትና ቴክኖሎጂ ቅድሚያ መስጠት ይገባል ብለዋል።

ግሮችን በዘላቂነት ለመፍታት አካታችነት የምርጫ ጉዳይ አይደለም ያሉት ምክትል ሊቀ መንበሯ፤ ሴቶች፣ አካል ጉዳተኞችና ሁሉንም የማህበረሰብ ክፍሎች ማሳተፍ እንደሚገባ ገልጸዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም