ቀጥታ፡

ለአየር ንብረት ለውጥ የማትበገር አፍሪካን ለመገንባት አህጉራዊ አንድነታችን ወሳኝ ነው - ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ተመስገን ጥሩነህ

አዲስ አበባ፤ ሚያዝያ 1/2018 (ኢዜአ)፡- ለአየር ንብረት ለውጥ የማትበገር አፍሪካን ለመገንባት አህጉራዊ አንድነታችን ወሳኝ ነው ሲሉ ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ተመስገን ጥሩነህ ገለጹ።

ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትሩ በማህበራዊ ትስስር ገጻቸው ባስተላለፉት መልዕክት ዛሬ በሰው ልጅ መገኛዋ ኢትዮጵያ፣ በአፍሪካውያን መሰባሰቢያ አዲስ አበባ፣16ኛውን የአፍሪካ የሥጋት መከላከል ዐቅም ጉባኤ (ARC-COP16) በይፋ አስጀምረናል ብለዋል።


 

አህጉራችን በአየር ንብረት ለውጥ ክፉኛ እየተፈተነች ትገኛለች ያሉት ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትሩ ፤ ሆኖም ይህ ፈተና ተስፋችንን የሚያጨልም፣ ጉዟችንን የሚገታ አይሆንም ሲሉም ገልጸዋል።

በእልህ፣ በቁጭትና በእንችላለን ኅብረት አንድነታችንን የምናጠናክርበት አጋጣሚ ነው።

እኛ አፍሪካውያን ከአደጋ በኋላ ለሚመጣ ርዳታ እጅ ከመዘርጋት ይልቅ፣ አደጋን ቀድሞ መከላከልና በሳይንሳዊ መንገድ ለመፍትሔ መዘጋጀት የህልውናችን መሠረት ሊሆን ይገባል ነው ያሉት።

ኢትዮጵያ በዚህ ረገድ ራዕይ ሰንቃ፣ ክንዷን አበርትታ ለአየር ንብረት ለውጥ የማይበገር ዐቅም እየገነባች መሆኑን ገልጸው፤ በአረንጓዴ ዐሻራ የምድርን ገጽታ እየቀየርን መሆኑንም ተናግረዋል።

በምግብ ሉዓላዊነት ንቅናቄ ራሳችንን ለመቻል እየተጋን ነው። በታዳሽ ኃይል ልማትም የአህጉራዊ ትሥሥር ገመድ እየሆንን ነው ብለዋል።

ሰው ሠራሽና የተፈጥሮ አደጋዎች በበዙበት፣ በአንጻሩ ዓለም አቀፋዊ ድጋፎች በቀነሱበት በዚህ ወቅት፣ የአፍሪካ ሥጋትን የመከላከል ዐቅም (African Risk Capacity-ARC) የመሰሉ አህጉራዊ ተቋሞቻችንን ማጠናከር አማራጭ የሌለው ጉዳይ መሆኑንም ገልጸዋል።

ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትሩ በመልዕክታቸው የአደጋ ሥጋትን በጥናት መለየት፣ ቀድሞ መከላከል፣ ችግር ሲከሠትም በአፍሪካዊ ዐቅም ምላሽ መስጠት ይገባል። ኢትዮጵያም ለዚህ የአፍሪካውያን ሌላኛው የሉዓላዊነት ግብ መሳካት በአርአያነት ትተጋለች ብለዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም