ቀጥታ፡

የወንጀል ሕግ ሥነ-ሥርዓት እና የማስረጃ ሕግ የፍትሕ ሥርዓቱን ወደ አዲስ ምዕራፍ የሚያሸጋግር ነው

አዲስ አበባ፤ ሚያዝያ 1/2018 (ኢዜአ)፡- አዲሱ የወንጀል ሕግ ሥነ-ሥርዓት እና የማስረጃ ሕግ የፍትሕ ሥርዓቱን ወደ አዲስ ምዕራፍ የሚያሸጋግር መሆኑን የሕጉ አርቃቂ ቡድን አባላት ገለጹ፡፡

የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት በ13ኛ መደበኛ ስብሰባው የኢትዮጵያ ፌዴራላዊ ዲሞክራሲያዊ ሪፐብሊክ የወንጀል ሕግ ሥነ-ሥርዓት እና የማስረጃ ሕግ ረቂቅ አዋጅን ማጽደቁ ይታወቃል።

ይህም የተቀላጠፈ የፍትሕ ሥርዓት እንዲኖር የሚያስችል፣ ልዩ የወንጀል ምርመራ ዘዴዎችን ያካተተና በተሳሳተ ማስረጃ ተፈርዶበት ታስሮ ለነበረ ግለሰብ ካሣ የሚከፈልበትን አግባብ የያዘ ዓለም አቀፍ መርሆዎችን የተከተለ መሆኑን በአዋጁ ላይ ተመላክቷል።

የሕጉ አርቃቂ ቡድን አባላት ከኢዜአ ጋር ባደረጉት ቆይታ፤ ሕጉ አዳዲስ ይዘቶችና ፋይዳዎችን በውስጡ የያዘ መሆኑ ገልጸዋል፡፡

የሕጉ አርቃቂ ቡድን አባል የሆኑት አቶ እሸቱ ወልደሰማዕት እንደገለጹት፣ ሕጉ የፌዴራል መንግሥት ሕግ ሲሆን እንዲሻሻል ካደረጉት ገፊ ምክንያቶች መካከል የወንጀል ሕጉ በተሟላ ሁኔታ ማስፈጸም መቻል ተጠቃሽ ነው ብለዋል፡፡

በተጨማሪም የፍትሕ ሥርዓቱን ከዘመኑ ጋር ለማዋጀት፣ ኢትዮጵያ የፈረመቻቸውን ዓለም አቀፍ ስምምነቶች ተፈጻሚ ለማድረግ እንዲሁም ሰብዓዊ መብቶችን ይበልጥ ማስከበር የሚሉት ይገኙበታል ብለዋል።

ሕጉ ከኢትዮጵያ የመንግሥት መዋቅር ጋር የተገናዘበ ግልጽ ዓላማና ግብ ያለው መሆኑን ጠቁመዋል።

ሕጉ እውነትን ማውጣት፣ የፍትሕ ስርዓት ሂደቱ ሕግን ተከትሎ እንዲፈጸም ማድረግ፣ የተቀላጠፈና እውነት ላይ የተመሰረተ ፍትሕ መስጠት እንዲሁም ሰብዓዊ መብትን ማስከበር የሚሉ ዋና ዋና ዓላማዎችን ያነገበ መሆኑን ተናግረዋል፡፡

በፌዴራሊዝም ሥርዓቱ መሠረት የክልል መንግሥታት ሕጉን በምን ዓይነት ሁኔታ ማስፈጸም እንዳለባቸው በዝርዝር የደነገገ መሆኑንም ጠቁመዋል፡፡


 

ሌላኛው የአርቃቂ ቡድኑ አባል ወይዘሮ ትዕግሥት መሀቤ በበኩላቸው ሕጉ ከ400 በላይ አንቀጾችን የያዘ ሰፊና በርካታ አዳዲስ ድንጋጌዎችን ያካተተ መሆኑን ተናግረዋል።

ሕጉ ባህላዊ የዳኝነት ሥርዓቶችን በአማራጭነት ማካተቱንም ጠቅሰዋል፡፡

ፍርድን መከለስ የሚያስችል ድንጋጌ ማካተቱንም ጠቅሰው፤ አንድ ተከሳሽ በተሳሳተ ማስረጃ ወይም የፍርድ ውሳኔ ከተላለፈበት በኋላ፣ ማስረጃው ስህተት መሆኑ ከተረጋገጠ ፍርዱ የሚከለስበትን አሠራር ማካተቱንም ነው የተናገሩት፡፡

እስካሁን ባለው አሠራር እንዲህ ዓይነት ችግር ሲያጋጥም ግለሰቦች በይቅርታ ብቻ ይወጡ እንደነበር አስታውሰው፤ አዲሱ ሕግ ግን ለተበዳዮች የካሣ ሥርዓት ጭምር መደንገጉን አረጋግጠዋል።


 

ሕጉ የፍትሕ ሥርዓቱን በጥራትና በዘመናዊነት ለመለወጥ የሚረዱ በርካታ ድንጋጌዎችን መያዙን የገለጹት ደግሞ ሌላኛው የአርቃቂ ቡድኑ አባል ውብሸት ሽፈራው (ዶ/ር) ናቸው።

ሕጉ ዝርዝር የክስ፣ የምርመራና የዳኝነት አካሄዶች በግልጽ መቀመጣቸውን ጠቅሰው፤ የማኅበረሰቡን የፍትሕ ፍላጎት ለማርካት ትኩረት የሰጡ ድንጋጌዎች መካተታቸውንም ገልጸዋል፡፡

በተለይም ከወንጀል ተጠያቂነት ጎን ለጎን የፍትሐ-ብሔር መፍትሔዎችን መስጠት የሚያስችሉ አሠራሮች መካተታቸው ጠቁመው፤ ይህም የፍትሕ ሥርዓቱን ይበልጥ ሰብዓዊነት እንዲኖርው መደረጉን ጠቅሰዋል፡፡

በአጠቃላይ አዲሱ የወንጀል ሕግ ሥነ-ሥርዓት እና የማስረጃ ሕግ በኢትዮጵያ የፍትሕ አስተዳደር ውስጥ የነበሩ ክፍተቶችን በመድፈን ውጤታማ የሕግ ማስከበር ሥራ እንዲኖር ፋይዳው የጎላ መሆኑ ተመልክቷል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም