ቀጥታ፡

ኢትዮጵያ እና ቡሩንዲ ጥልቅ የሆነ የወንድማማችነትና የጋራ መከባበር ታሪክ ያላቸው ሀገራት ናቸው - ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ(ዶ/ር)

አዲስ አበባ፤ ሚያዝያ 1/2018 (ኢዜአ) ፦ ኢትዮጵያ እና ቡሩንዲ ጥልቅ የሆነ የወንድማማችነትና የጋራ መከባበር ታሪክ ያላቸው ሀገራት ናቸው ሲሉ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ገለጹ።

ጠቅላይ ሚኒስትሩ ለይፋዊ ጉብኝት አዲስ አበባ ለገቡት የቡሩንዲ ፕሬዝዳንት ኤቫሪስቴ ንድያይሺሚዬ አቀባበል አድርገዋል።


 

ይሄንን አስመልክቶ ጠቅላይ ሚኒስትሩ በማህበራዊ ትስስር ገጻቸው የቡሩንዲ ሪፐብሊክ ፕሬዝዳንት ክቡር ኤቫሪስቴ ንድያይሺሚዬ፤ በድንቅ ህዝቦቿና ባህሏ ወደ ምትቀበሎት ሀገሬ ኢትዮጵያ እንኳን በሰላም መጡ ስል በታላቅ ክብር ነው በማለት ገልጸዋል።

ኢትዮጵያ እና ቡሩንዲ ጥልቅ የሆነ የወንድማማችነትና የጋራ መከባበር ታሪክ ያላቸው ሲሆን በሁለቱ ሀገራት መካከል ያለውን ዘላቂ ትስስርም በከፍተኛ ሁኔታ እንደምናከብር ላስታውሶት እወዳለሁ ብለዋል።


 

በዚህ ይፋዊ የስራ ጉብኝትዎ፣ ለወደፊቱ ያለንን የጋራ ትልም ወደ እውነት ለመቀየር በምናደርገው ጥረት፤ ቆይታዎ ግንኙነታችንን የበለጠ እንደሚያጠናክረው አልጠራጠርም ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ በድጋሚ እንኳን ወደ ሁለተኛ ቤትዎ እንኳን በደህና መጡ ለማለት እወዳለሁ ሲሉም ገልጸዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም