በለውጡ ዓመታት የተገኙ የልማት ስራዎችን ለማስቀጠል የድርሻችንን እንወጣለን-የሰመራ ሎጊያ ከተማ ነዋሪዎች - ኢዜአ አማርኛ
በለውጡ ዓመታት የተገኙ የልማት ስራዎችን ለማስቀጠል የድርሻችንን እንወጣለን-የሰመራ ሎጊያ ከተማ ነዋሪዎች
ሰመራ፣ሚያዝያ 1/2018 (ኢዜአ) ፡-በለውጡ ዓመታት የተገኙ የልማት ስራዎችን ለማስቀጠል የድርሻቸውን እንደሚወጡ የሰመራ ሎጊያ ከተማ ነዋሪዎች ተናገሩ።
የሀገራዊ ለውጡን 8ኛ ዓመት በማስመልከት ህዝባዊ የድጋፍ ሰልፍ በሠመራ ስታዲየም በዛሬው ዕለት ተካሂዷል።
በድጋፍ ሰልፉ ላይ ከተሳተፉ የሰመራ ሎጊያ ከተማ ነዋሪዎች መካከል አቶ አሃው ሻሚ እንደተናገሩት ሀገራዊ ለውጡን በመደገፍና ትሩፋቶቹን ለማስቀጠል በድጋፍ ሰልፉ ተሳትፈዋል።
ለውጡ እውነተኛ ፌዴራሊዝምን በመተግበር የህዝቦች አንድነት የተጠናከረበት መሆኑን ገልፀው ከዚህ ጎን ለጎን በለውጡ ዓመታት ሀገራዊ ፋይዳው የጎላ ሁለንተናዊ ልማት መከናወኑን ገልፀዋል።
ሌላዋ የድጋፍ ሰልፉ ተሳታፊ ወይዘሮ መዲና መሐመድ በበኩላቸው እንዳሉት በስምንት የለውጡ ዓመታት የተሰሩ ስራዎች የሀገርን ገጽታ የቀየሩ ናቸው።
ይህም ከተረጂነት ለመውጣት የሚደረገውን ጥረት ለማሳካት መሰረት የሚጥሉና የህዝብን ሁለንተናዊ ተጠቃሚነት ያረጋገጡ መሆናቸውን ጠቁመዋል።
በለውጡ አመታት ከተከናወኑ ተግባራት መካከል በተለይ የከተሞች የኮሪደር ልማት የዜጎችን ኢኮኖሚያዊ ተጠቃሚነትና የከተሞችን ገጽታ በመቀየር ተጨማሪ አቅም መፍጠራቸውን አንስተዋል።
አቶ መሐመድ ያዮ በበኩላቸው ባለፉት ስምንት የለውጥ ዓመታት የህዝብን የልማትና መልካም አስተዳደር ጥያቄዎች ምላሽ የሰጡ ስራዎች ተሰርተዋል ብለዋል።
ይህም የህብረተሰቡን ልማት የማስቀጠል ተነሳሽነትን የፈጠረና በመተባበር መለወጥ እንደሚቻል ያሳየ መሆኑን ገልጸው፤ እሳቸውም ልማቱ ተጠናክሮ እንዲቀጥል የድርሻቸውን እንደሚወጡም አረጋግጠዋል።