ዲጂታል ኢንሼቲቩ ለኢኮኖሚያዊና ማህበራዊ እድገት መፋጠን ያለው ፋይዳን በመገንዘብ በባለቤትነት መንፈስ ሊተገበር ይገባል -ርዕሰ መስተዳድር አረጋ ከበደ - ኢዜአ አማርኛ
ዲጂታል ኢንሼቲቩ ለኢኮኖሚያዊና ማህበራዊ እድገት መፋጠን ያለው ፋይዳን በመገንዘብ በባለቤትነት መንፈስ ሊተገበር ይገባል -ርዕሰ መስተዳድር አረጋ ከበደ
ባህርዳር፤ ሚያዚያ 1/2018 (ኢዜአ)፦ የክልሉ አመራር ዲጂታል ኢንሼቲቩ ለኢኮኖሚያዊና ማህበራዊ እድገት መፋጠን ያለው ፋይዳ በመገንዘብ በባለቤትነት መንፈስ ሊተገብረው እንደሚገባ የአማራ ክልል ርዕሰ መስተዳድር አቶ አረጋ ከበደ አሳሰቡ።
ርዕሰ መስተዳድሩ በክልሉ መሶብ የአንድ ማዕከል አገልግሎት፣ የፋይዳ ዲጂታል መታወቂያና ኢትዮ ኮደርስ አፈጻጸም ያለበትን ሁኔታ በመገምገም ቀጣይ የስራ መመሪያ አስተላልፈዋል።
ርዕሰ መስተዳድር አረጋ በመድረኩ ላይ ባስተላለፉት መልእክት የመንግስት ተቋማትን አሰራር ፈጣንና ቀልጣፋ ለማድረግ የዲጂታል አሰራርን መተግበር ይገባል ብለዋል።
በክልሉ መሶብ የአንድ ማዕከል አገልግሎት፣ ፋይዳ ዲጂታል መታወቂያና ኢትዮ ኮደርስ ኢንሼቲቮች የዲጂታል ትራንስፎርሜሽኑን የሚያረጋግጡ መሆናቸውን ገልጸዋል።
አመራሩም ኢንሼቲቮቹ ለኢኮኖሚያዊና ማህበራዊ እድገት መፋጠን ያላቸውን ፋይዳ በመገንዘብ በባለቤትነት መንፈስ ሊተገብራቸው እንደሚገባም አስገንዝበዋል።
የትምህርትና ጤና ሴክተር ሰራተኞችን ጨምሮ ሁሉም የመንግስት ሰራተኞች በዲጂታል መታወቂያ ምዝገባ ላይ በንቃት መሳተፍ እንዳለባቸው አመልክተዋል።
የዲጂታል ትግበራው አገልግሎት አሰጣጥን ለማሻሻል፣ የዜጎችን ደህንነት ለማረጋገጥ፣ አለም አቀፍ ተወዳዳሪነትን ለማጎልበት በተሟላ ሁኔታ መተግበር አለበት ብለዋል።
በምክትል ርዕሰ መስተዳደር ማዕረግ የአማራ ክልል የከተማ ዘርፍ አስተባባሪ አህመዲን መሀመድ (ዶ/ር) በበኩላቸው እየተተገበሩ የሚገኙት ኢንሸቲቮች የክልሉን የዲጂታል ትራንስፎርሜሽን ጉዞ የሚያፋጥኑ ሞተሮች መሆናቸውን ተናግረዋል።
መሶብ የአንድ ማዕከል አገልግሎት በርካታ ተቋማት በአንድ ማእከል አገልግሎታቸውን ለህብረተሰቡ በማቅረብ ይነሳ የነበረውን የመልካም አስተዳደር ችግር ለመቅረፍ ማስቻሉን አክለዋል።
ፋይዳ የዲጂታል መታወቂያን እስካሁን 5 ነጥብ 3 ሚሊዮን የክልሉ ነዋሪዎች መውሰዳቸውን ጠቁመው፤ በቀጣይ ሦስት ወራትም ቀሪ ግቦችን ለማሳካት የተጀመሩ ተግባራት ተጠናክረው እንደሚቀጥሉም አረጋግጠዋል።
የክልሉ ሲቪል ሰርቪስና ሰው ሃብት ልማት ቢሮ ሃላፊ ወይዘሮ ባንችአምላክ ገብረማሪያም፤ መሶብ የአንድ ማዕከል አገልግሎት፣ የኢትዮ ኮደርስና የፋይዳ ዲጂታል መታወቂያ ዲጂታል ኢትዮጵያ 2030ን ለማሳካት እንደሚያስችሉ አስረድተዋል።
በመድረኩ ላይ ዘርፎቹን የሚመሩ አመራሮችና ሌሎች ባለድርሻ አካላት ተገኝተዋል።