ለትንሳኤ በዓል የግብርና እና የኢንዱስትሪ ምርቶችን በስፋትና በተመጣጣኝ ዋጋ እያገኘን ነው- ሸማቾች - ኢዜአ አማርኛ
ለትንሳኤ በዓል የግብርና እና የኢንዱስትሪ ምርቶችን በስፋትና በተመጣጣኝ ዋጋ እያገኘን ነው- ሸማቾች
አዲስ አበባ፤ ሚያዝያ 1/2018(ኢዜአ)፡- በመዲናዋ ለትንሳኤ በዓል የግብርና እና የኢንዱስትሪ ምርቶችን በስፋትና በተመጣጣኝ ዋጋ እያገኙ መሆኑን አስተያየታቸውን ለኢዜአ የሰጡ ሸማቾች ገለጹ።
ኢዜአ ለበዓል ፍጆታ የሚያስፈልጉ ልዩ ልዩ የግብርና እና የኢንዱስትሪ ምርቶች አቅርቦት ምን እንደሚመስል የህብረት ስራ ዩኒየኖችና ሸማች ህብረት ስራ ማህበራት የመሸጫ ሱቆች እና መደብሮች ቅኝት አድርጓል፡፡
ቅኝት ባደረገባቸው የሸማች ህብረት ስራ ማህበራትና ዩኒየኖች ለበዓል ፍጆታ የሚያስፈልጉ ምርቶች ማቅረባቸውንና ህብረተሰቡም ሲገበያይ መመልከት ችሏል።
የብርሃን ለሸማቾች ህብረት ስራ ማህበር ስራ አስኪያጅ አቶ ይታየው ታደለ ለኢዜአ እንደገለጹት ለትንሳኤ በዓል ተፈላጊ የሆኑ የግብርና እና የኢንዱስትሪ ምርቶች ለማቅረብ ቀደም ተብሎ ዝግጅት ሲደረግ ቆይቷል።
ከአምራቾች ጋር ትስሰር በመፍጠርና በዩንዮኖች በኩል ያለ ደላላ ጣልቃ ገብነት በቂ ምርት ወደ ህብረት ስራ ማሀበራት ማስገባት መቻሉን አስታውቀዋል፡፡
ይህን ተከትሎ ለትንሳኤ በዓል ዘይት ዱቄት፤ ሽንኩርት ፤እንቁላል እና ሌሎችም ለበዓሉ አስፈላጊ የሆኑ ምርቶችን በስፋት እና በተመጣጣኝ ዋጋ እያቀረቡ እንደሚገኙ አስታውቀዋል፡፡
አውቶቡስ ተራ ሁለገብ ሸማች ሃላፊነቱ የተወሰነ ህብረት ስራ ማህበር ስራ አስኪያጅ አቶ አንዷለም አስማረ በበኩላቸው፤ ለበዓሉ አስፈላጊ የሆኑ የባልትና ውጤቶችን ጨምሮ ሌሎችን ምርቶች በተመጣጣኝ ዋጋ ለህብረተሰቡ እየተከፋፈለ መሆኑን ተናግረዋል፡፡
የብስራት ለጉለሌ ዩኒየን ዋና ስራ አስኪያጅ ሞገስ መንገሻ በዩኒየኑ ባሉት 10 መሰረታዊ ህብረት ስራ ማህበራት በኩል ምርቶቹን ለመሰረታዊ ማህበራትና ለህብረት ስራ ማህበራቱ በጅምላ እየተከፋፈለ መሆኑን ተናግረዋል፡፡
በማህበራቱ ሲሸምቱ ያገኘናቸው ሸማቾች በበኩላቸው፤ ለበዓሉ ተፈላጊ የሆኑ የግብርና እና የኢንዱስትሪ ምርቶችን በተመጣጣኝ ዋጋ እያገኙ መሆናቸውን ገልጸዋል።
ካነጋርናቸው ሸማቾች መካከል ወይዘሮ ዓለም ለገሰ እንዳሉት ከዘይት ጀምሮ ለበዓል ተፈላጊ የሚባሉ ሽንኩርትና የተለያዩ ግብዓቶች በተመጣጠነ ዋጋ ማግኘታቸውን ተናግረዋል፡፡
ሌላኛዋ ሸማች ወይዘሮ ጤና ይበልጣል በበኩላቸው በሸማቾች በኩል ለበዓሉ የሚያስፈልጉ የተለያዩ ምርቶችን ማግኘታቸውን አንስተዋል፡፡
መንግሥት በህብረት ሥራ ማህበራት አማካኝነት ምርቶችን በተመጣጣኝ ዋጋ በማቅረብ የገበያ መረጋጋት ለመፍጠር ያከናወናቸው ተግባራት የሚደነቁ መሆኑን የተናገሩት ደግሞ ወይዘሮ ፍሬህይወት አባይነህ እና ብዙአየሁ አበበ ናቸው፡፡