የኢትዮጵያ መከላከያ ሰራዊት ለአፍሪካ ኩራት ነው - ኢዜአ አማርኛ
የኢትዮጵያ መከላከያ ሰራዊት ለአፍሪካ ኩራት ነው
አዲስ አበባ፤ ሚያዝያ 1/2018 (ኢዜአ)፡- የኢትዮጵያ መከላከያ ሰራዊት የሀገሩን ሉዓላዊነት ከማስጠበቅ ባለፈ ለአፍሪካ ኩራት ነው ሲሉ የብሩንዲ ፕሬዚዳንትና የወቅቱ የአፍሪካ ሕብረት ሊቀመንበር ኤቫሪስት ንዳይሽሚዬ ገለጹ።
ፕሬዚዳንት ኤቫሪስት ንዳይሽሚዬ ዛሬ በኢፌዴሪ መከላከያ ሚኒስቴር ጉብኝት አድርገዋል።
ከጉብኝታቸው በኋላም ከመከላከያ ሚኒስትር አይሻ መሐመድ (ኢ/ር) ጋር የሁለትዮሽ ውይይት አድርገዋል።
በዚሁ ወቅትም፤ በሁለቱ ሀገራት መካከል ያለውን ወታደራዊ ትብብር ይበልጥ ማጠናከር በሚቻልባቸው ሁኔታዎች ላይ ሰፊ ምክክር ማድረጋቸውን የመከላከያ ኦንላይን ሚዲያ ለኢዜአ የላከው መረጃ አመላክቷል።
ፕሬዚዳንቱ በውይይታቸው ላይ፤ ብሩንዲ የሰላም ዕጦት ውስጥ በነበረችበት ወቅት የኢትዮጵያ መከላከያ ሰራዊት ሰላም በማስከበር ረገድ ላበረከተው ሚናና ለከፈለው መስዋዕትነት የላቀ ምስጋና አቅርበዋል።
የኢትዮጵያ መከላከያ ሰራዊት የሀገሩን ሉዓላዊነት ከማስጠበቅ ባለፈ ለአፍሪካ ኩራት የሆነ ሰራዊት መሆኑንም በማንሳት አድናቆታቸውን ገልፀዋል።
የሁለቱ ሀገራት መከላከያ ሰራዊት አባላት በሶማሊያ ሰላም የማስከበር ተልዕኮ ላይ በጋራ ውጤታማ ተግባራትን ማከናወናቸውን አስታውሰው፤ ኢትዮጵያ ለብሩንዲ ሰራዊት በስልጠና እና በተለያዩ ድጋፎች ስታደርግ የቆየችውን አስተዋፅኦ አድንቀዋል።
በርካታ የብሩንዲ ሰራዊት አባላትም በኢትዮጵያ ስልጠና በመውሰድና አቅማቸውን በመገንባት ወደ ሀገራቸው መመለሳቸውን በመጥቀስ፤ አሁንም የብሩንዲ መከላከያ ሰራዊት የኢትዮጵያን ድጋፍና ልምድ እንደሚፈልግ ተናግረዋል።
ይህ ጉብኝት በሁለቱ ሀገራት መካከል ያለውን ወታደራዊ ትብብር ወደ ላቀ ደረጃ እንደሚያሸጋግረው ፕሬዚዳንቱ ያላቸውን እምነት ገልፀዋል።
የመከላከያ ሚኒስትር አይሻ መሐመድ (ኢ/ር) በበኩላቸው፤ የፕሬዚዳንቱ ጉብኝት በሁለቱ ሀገራት መካከል ያለውን ጥብቅ አጋርነት የሚያሳይ ጉልህ ምልክት መሆኑን ተናግረዋል።
ጉብኝቱ ትብብሩን ይበልጥ ለማጠናከርና ሙያዊ ልምዶችን ለመለዋወጥ ወሳኝ አጋጣሚ መሆኑንም አክልዋል።
በተለይም በሁለቱ ሀገራት የመከላከያ ተቋማት መካከል ያለውን ወታደራዊ ትብብር ይበልጥ ለማሳደግ፣ በወታደራዊ ኢንዱስትሪ መስኮችና በጋራ ወታደራዊ ስልጠናዎች ላይ በትኩረት ለመስራት ዝግጁነት መኖሩንም ጠቁመዋል።
ይህ ትብብርም የሁለቱን ሀገራት የጋራ ደህንነት ከማረጋገጥ ባለፈ ለቀጣናዊ ሰላም መጠበቅ ያለውን አህጉራዊ ኃላፊነት በጋራ ለመወጣት የሚያስችል ወሳኝ እርምጃ ነው ሲሉ ገልፀዋል፡፡