ቀጥታ፡

የምስራቅ ቦረና ዞን የነዳጅና የግብርና ምርቶችን በህገወጥ መንገድ የሚያዘዋውሩ አካላትን የመቆጣጠር ተግባሩን አጠናክሯል

ነገሌ ቦረና፤ሚያዝያ 1/2018 (ኢዜአ)፡- የምስራቅ ቦረና ዞን  የነዳጅና የግብርና ምርቶችን በህገወጥ መንገድ የሚያዘዋውሩ አካላትን የመቆጣጠር ተግባር ማጠናከሩን የዞኑ አስተዳደር አስታወቀ።

በህገወጥ የነዳጅና የግብርና ምርቶች ዝውውር ላይ ያተኮረ የምክክር መድረክ በነገሌ ቦረና ከተማ ተካሄዷል፡፡

በዚሁ ወቅት የዞኑ ዋና አስተዳዳሪ አቶ አብዱረዛቅ ሁሴን፤ በዞኑ የሚገኙ አንዳንድ ነጋዴዎች በአቋራጭ ለመበልጸግ ምርት በመደበቅ ተገቢ ያልሆነ የዋጋ ጭማሪ እያደረጉ ይገኛሉ። 

በተለይም ወቅታዊ ሁኔታውን ምክንያት በማድረግ በህገወጥ መልኩ ነዳጅን የሚያዘዋውሩ አካላት መኖራቸውም ተረጋግጧል ብለዋል።

ለዚህም የዞኑ አስተዳደር ግብረ ኃይል አቋቁሞ ከማደያ ውጭ ነዳጅ በሚሸጡ ህገወጦች ላይ ጠንካራ ክትትልና ቁጥጥር እያደረገ መሆኑን ገልጸዋል። 

እስካሁን በተደረገው ጥረትም በርካታ የንግድ ድርጅቶች መታሸጋቸውን፣ የተወሰኑ የንግድ ቤቶች ባለቤቶችም በቁጥጥር ስር ውለው ተጠያቂ መሆናቸውን ተናግረዋል።

በቀጣይም ህብረተሰቡ ያልተገባ የንግድ እንቅስቃሴ እንዲሁም ህገወጥ የምርት እና የሸቀጦች ዝውውር ሲመለከት ለሚመለከተው አካል ጥቆማ እንዲሰጥ ጥሪ አቅርበዋል። 

በሌላ በኩል በንግዱ ማህበረሰብ ላይ ያልተገባ ድርጊት ሲፈጽሙ የተገኙ የመንግስት ሰራተኞችም ተጠያቂ እየተደረጉ መሆኑንም ጠቁመዋል።

የዞኑ ንግድ ጽህፈት ቤት ኃላፊ አቶ ገልማ ገልገሎ፤ ህገወጥ የንግድ እንቅስቃሴን ለመከላከል ከዞን አስተዳደር፣ ከንግድ፣ ከአቃቤ ህግ፣ ከፖሊስና ከሌሎችም ተቋማት የተውጣጣ የክትትልና ቁጥጥር ኮሚቴ ተቋቁሞ የተለያዩ ተግባራትን እያከናወነ ይገኛል ብለዋል።

ምርት የደበቁ፣ ፍትሀዊ ያልሆነ የዋጋ ጭማሪ ባደረጉና በኮንትሮባንድ ስራ ላይ የተሰማሩ ነጋዴዎች ላይ ህጋዊና አስተዳደራዊ እርምጃ እየተወሰደ መሆኑን ገልጸዋል፡፡

በተጨማሪም 177 ሚሊዮን ብር ግምት ያለው የኮንትሮባንድ እቃ ሲያዘዋውሩ የተገኙ 62 ግለሰቦች ፍርድ ቤት መቅረባቸውን ተናግረዋል፡፡ 

በሀገር ውስጥ ምርቶች ላይ ፍትሀዊ ያልሆነ ዋጋ በሚጨምሩ የንግድ ድርጅቶች ላይ የሚወሰደው እርምጃ ተጠናክሮ እንደሚቀጥልም አስታውቀዋል። 

 

የነዳጅ ምርት በተቀመጠው አቅጣጫ መሰረት ቅድሚያ ማግኘት የሚገባቸው አካላት እንዲያገኙ ጥብቅ ቁጥጥር እየተደረገ መሆኑንም አስረድተዋል።

 

በውይይት መድረኩ ላይ የተሳተፉት የነገሌ ቦረና ከተማ ነዋሪው አቶ ግዛቸው ካሳ፤ በህገወጦች ላይ የተጀመረው ክትትልና ቁጥጥር ተጠናክሮ መቀጠል አለበት ብለዋል። 

 

ሌላዋ የመድረኩ ተሳታፊ ወይዘሮ አይናለም አየለ በበኩላቸው፤ የዞኑ አስተዳደር ህገወጥነት ላይ የጀመረው ቁጥጥር ውጤታማ እንዲሆን የበኩላቸውን እንደሚወጡም አረጋግጠዋል።

 

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም