በምዕራብ ጎንደር ዞን ቋራ ወረዳ በህገ ወጥ መንገድ ተከማችቶ የተገኘ 12 በርሜል ነዳጅ በቁጥጥር ስር ዋለ - ኢዜአ አማርኛ
በምዕራብ ጎንደር ዞን ቋራ ወረዳ በህገ ወጥ መንገድ ተከማችቶ የተገኘ 12 በርሜል ነዳጅ በቁጥጥር ስር ዋለ
ገንዳውኃ፣ ሚያዝያ 1/2018 (ኢዜአ)፦ በምዕራብ ጎንደር ዞን ቋራ ወረዳ በህገ ወጥ መንገድ ተከማችቶ የተገኘ 12 በርሜል ነዳጅ በቁጥጥር ስር ማዋሉን የወረዳው ፖሊስ አስታወቀ።
በመካከለኛው ምስራቅ ጦርነት ምክንያት የተከሰተውን የነዳጅ አቅርቦት ችግር ለመቋቋም በመንግስት በኩል ግብረ ሃይል ተቋቁሞ የተለያዩ የመፍትሄ እርምጃዎች እየተወሰዱ መሆኑ ይታወቃል።
የነዳጅን አጠቃቀምን በቁጠባ ከማድረግ በተጓዳኝ የነዳጅን ግብይት ሕገ-ወጥ እንቅስቃሴን መቆጣጠርና ጥብቅ ክትትል ማድረግ እንደሚገባም ተመላክቷል።
በዚህም መሰረት በአማራ ክልል በምዕራብ ጎንደር ዞን ቋራ ወረዳ በህገ ወጥ መንገድ ተከማችቶ የተገኘ 12 በርሜል ነዳጅ በቁጥጥር ስር ማዋሉን የወረዳው ፖሊስ አስታውቋል።
በወረዳው ፖሊስ ጽህፈት ቤት የወንጀል ምርመራ ክፍል ኃላፊ ኢንስፔክተር ፍቅሩ አባይ፤ በህገ ወጥ መልኩ ተከማችቶ የተገኘው ነዳጅ በገለጉ ከተማ በሁለት ግለሰቦች በመኖሪያ ቤት መሆኑን ተናግረዋል።
በመሆኑም በህዝብ ጥቆማ በተደረገው ክትትል የነዳጅ ምርቱን ከነተጠርጣሪ ግለሰቦቹ ፖሊስ በቁጥጥር ስር ማዋሉን ገልጸዋል።
ግለሰቦቹ በህገ ወጥ መንገድ ለመክበር በመፈለግ በሀገርና በህዝብ ላይ ጉዳት ለማድረስ የፈጸሙት መሆኑን አንስተው በቀጣይም ጥብቅ ቁጥጥር የማድረግና ተጠርጣሪዎችን በህግ ተጠያቂ የማድረግ ስራ ይቀጥላል ብለዋል።