በጉራጌ ዞን በዓልን ተከትሎ ያልተገባ የዋጋ ጭማሪ እንዳይደረግ ቁጥጥር እየተደረገ ነው - ኢዜአ አማርኛ
በጉራጌ ዞን በዓልን ተከትሎ ያልተገባ የዋጋ ጭማሪ እንዳይደረግ ቁጥጥር እየተደረገ ነው
ወልቂጤ፤ ሚያዝያ 1/2018 (ኢዜአ)፦ በጉራጌ ዞን በዓልን ተከትሎ ያልተገባ የዋጋ ጭማሪ እንዳይደረግ ቁጥጥር እየተደረገ መሆኑን የዞኑ ንግድና ገበያ ልማት መምሪያ ገለጸ።
የትንሳኤ በዓልን አስመልክቶ በዞኑ ያልተገባ የዋጋ ጭማሪ እንዳይኖር የቅዳሜና እሁድ ገበያዎችን በማጠናከር የፍጆታ ምርቶች ለሸማቾች በተመጣጣኝ ዋጋ እየቀረቡ መሆናቸው ተመላክቷል።
የጉራጌ ዞን ንግድና ገበያ ልማት መምሪያ ኃላፊ አቶ መኩሪያ ተመስገን እንደገለጹት፤ የትንሳኤ በዓልን ተከትሎ ያልተገባ የዋጋ ጭማሪ እንዳይከሰት በትኩረት እየተሰራ ነው።
ለዚህም በመንግስት እና በግል የንግድ ድርጅቶች ጋር በመቀናጀት እየተሰራ ባለው ተግባር የእርድ እንስሳት፣ ዘይት፣ ስኳር፣ የዳቦ ዱቄትና ሌሎች መሰረታዊ የኢንዱስትሪና የግብርና ምርቶችን በበቂ ሁኔታ ማቅረብ መቻሉን ጠቁመዋል።
በዞኑ የተቋቋሙ ከ37 በላይ የቅዳሜና እሁድ ገበያዎች ዘወትር ጭምር አገልግሎት እንዲሰጡ በማድረግ በበቂ ሁኔታ ምርት እንዲቀርብ የማድረግ ስራ መከናወኑን አስረድተዋል።
ከነዳጅ እጥረት የተነሳ የምርት አቅርቦት እንዳይስተጓጎል በዘርፉ ለተሰማሩ አሽከርካሪዎች ነዳጅ ቅድሚያ እንዲያገኙ በማድረግ የግብርናና የፋብሪካ ምርት እንዲቀርብ እየተደረገ ነው ብለዋል።
የቅዳሜና እሁድ ገበያዎችን አጠናክሮ ከማስቀጠል ባለፈ ሳምንቱን ሙሉ አገልግሎት በመስጠት ለሸማቹ ማህበረሰብ የተለያዩ የአትክልት ምርቶች እየቀረቡ መሆኑን የሚናገሩት በወልቂጤ ከተማ በአትክልትና ፍራፍሬ ንግድ የተሰማሩት ወይዘሮ ዘይነባ አወል ናቸው።
ለበዓል የሚሆን በቂ ምርት ማቅረባቸውን አስረድተው በተመጣጣኝ ዋጋ እየሸጡ መሆናቸውን ተናግረዋል።
በከተማው ሲገበያዩ ያገኘናቸው አቶ አስማማው ገብረማርያም በሰጡት አስተያየት፤ የእርድ እንስሳት፣ እንቁላልና አንዳንድ ለበዓል የሚያስፈልጉ ምርቶች ዋጋ ካለፉት ዓመታት መጠነኛ ጭማሪ ቢኖረውም የተሻለ አቅርቦት መኖሩን ገልጸዋል።
የምርት አቅርቦቱ እና ገበያ ለማረጋጋት የተሰራው ስራ ሸማቹ በአቅሙ ልክ የሚፈልገውን ገዝቶ በዓሉን በደስታ ለማሳለፍ የሚያስችል ነው ብለዋል።
በዓልን ምክንያት በማድረግ የቀረቡ የግብርና ምርቶች አምራቹ በቀጥታ ከማሳው ወደ ተጠቃሚው እንዲቀርብ ለማድረግ ጥረት መደረጉ ማሳያ ናቸው ያሉት ደግሞ ሌላኛው ሸማች አቶ ታረቀኝ ሀብቴ ናቸው።
ለበዓሉ የሚሆኑ መሰረታዊ የፍጆታ ምርቶች ለሸማቹ በበቂ ሁኔታ መቅረባቸውን በመግለጽ፣ በአንዳንድ ምርቶች ላይ አምና ከነበረው ተመሳሳይ ወቅት ጋር ሲነፃፀር የተወሰነ ጭማሪ መኖሩን ተናግረዋል።