በክልሉ በተለያዩ አካባቢዎች ለትንሳኤ በዓል የሚያስፈልጉ ምርቶች በተሻለ ሁኔታ ቀርበዋል - ኢዜአ አማርኛ
በክልሉ በተለያዩ አካባቢዎች ለትንሳኤ በዓል የሚያስፈልጉ ምርቶች በተሻለ ሁኔታ ቀርበዋል
አዲስ አበባ፤ ሚያዝያ 1/2018(ኢዜአ)፡- በኦሮሚያ ክልል በተለያዩ አካባቢዎች ለትንሳኤ በዓል የሚያስፈልጉ ምርቶች በተሻለ ሁኔታ መቅረባቸውን ሻጮችና ሸማቾች ተናገሩ።
የጅማ ከተማ ነዋሪው አቶ ባህሩ ታረቀኝ ለበዓል ገበያው አስፈላጊ የኢንዱስትሪ እና የግብርና ምርቶች መቅረባቸውን ገልጸው፣ በልዩ የበዓል ገበያው ከመደበኛው ዋጋ ባነሰ እየሸመትን ነው ብለዋል።
ሌላኛዋ ነዋሪ ረድኤት አማረ ለበዓሉ አስፈላጊ የሆኑ ግብዓቶችን በተመጣጣኝ ዋጋ መሸመቷን ትናገራለች።
ከወቅታዊ ሁኔታዎች አንጻር ትልቅ ስጋት እንደነበራት ተናግራ፤ ነገር ግን እንደታሰበው ሳይሆን የተሻለ አቅርቦት በመኖሩ በበቂ መሸመቷን ገልጻለች።
መሰል የበዓል ገበያዎች ቀደም ብሎ ታቅደው መዘጋጀታቸው ለማህበረሰቡ የተሻለ መሆኑን የተናገሩት ደግሞ የጅማ ከተማ ነዋሪዋ ወይዘሮ ፀሐይነሽ ካሳ ናቸው።
እንደ ወይዘሮ ፀሐይነሽ ገለጻ ሽንኩርት በ90 ብር፣ቲማቲም በተመጣጣኝ ዋጋ መግዛታቸውን የገለጹ ሲሆን ዘይት ከመደበኛው ገበያ በ300 ብር ቅናሽ መግዛታቸውን ተናግረዋል።
በሸገር ከተማም ለትንሳኤ በዓል የተለያዩ ምርቶችና ሸቀጦችን ያቀረቡ ነጋዴዎች የበዓል ገበያው የተሻለ አቅርቦት ያለበት መሆኑን ተናግረዋል።
በመልካ ኖኖ ክፍለ ከተማ ለበዓሉ ምርቶችን እያቀረበ ያለው አቶ ኬር መሃመድ አሊ እንደተናገሩት፣ ለዘንድሮ የትንሳኤ በዓል ከነዳጅ ጋር ተያይዞ የመጓጓዣ ሁኔታ ፈታኝ ቢሆንም የአቅርቦት እጥረት የለም።
በተለይም ቀይና ነጭ ሽንኩርት፣ ቲማቲምና ሌሎች የግብርና ምርቶች ከአምናው በተሻለ መልኩ በተመጣጣኝ ዋጋ ለህብረተሰቡ እያቀረብን ነው ብለዋል።
በክፍለ ከተማው በማህበር ተደራጅተው የእንቁላል ምርት ለበዓሉ በተመጣጣኝ ዋጋ እያቀረቡ መሆኑን የተናገረው ደግሞ ወጣት አማኑኤል ጫላ ነው።
ሌላው የአትክልትና ፍራፍሬ አቅራቢ አቶ ግርማ በቀለ፣ ዘንድሮ ብዛት ያለው ምርት መኖሩን ጠቅሰው፣ በተለይም ለበዓል ፍጆታ የሚውሉ ምርቶችን የህብረተሰቡን ኪስ ባልጎዳ መልኩ በተመጣጣኝ ዋጋ ለማቅረብ ጥረት እያደረግን ነው ብለዋል።
አሁን ላይ ያለው የገበያ ሁኔታ አስደሳች ነው ያሉት አቶ ግርማ፣ ህብረተሰቡም በተሻለ ሁኔታ ምርቱን እየተጠቀመ ይገኛል ብለዋል።
የምስራቅ ሸዋ ዞን የህብረት ስራ ማስፋፊያ ኤጀንሲ በበኩሉ መጪውን የትንሳኤ በዓል ምክንያት በማድረግ በቂ የእርድ እንስሳትና እህል ለገበያ መቅረቡን ገልጿል።
የዞኑ የህብረት ስራ ማስፋፊያ ኤጀንሲ ኃላፊ አቶ አስራት ጌቱ እንደገለጹት፣ በዞኑ የትንሳኤ በዓል ገበያ የተረጋጋ እንዲሆን ከሉሜ አዳማ፣ መቂ ባቱና ቦራ ደንበል ዩኒየኖች እንዲሁም ከመሰረታዊ ማህበራት ጋር በመተባበር በቂ ምርት እንዲቀርብ እየተደረገ ነው ብለዋል።
በተለይም ሸማቹ የግብርና እና የኢንዱስትሪ ምርቶችን ቀጥታ ከሻጩ እንዲያገኝ እየተደረገ መሆኑን ጠቅሰው፣ በሉሜ አዳማ የህብረት ስራ ዩኒየን በኩል የደለቡ በሬዎች ለገበያ መቅረባቸውን ገልጸዋል።
በተመሳሳይ ጤፍ፣ የስንዴ ዱቄት፣ ሽንኩርትና ቲማቲም ለበዓል ገበያው በተመጣጣኝ ዋጋ መቅረባቸውን ጠቁመዋል።