በደብረ ብርሀን ከተማ ለትንሳኤ በዓል የግብርናና የኢንዱስትሪ ምርቶች በበቂ ሁኔታ ቀርበዋል - ኢዜአ አማርኛ
በደብረ ብርሀን ከተማ ለትንሳኤ በዓል የግብርናና የኢንዱስትሪ ምርቶች በበቂ ሁኔታ ቀርበዋል
ደብረ ብርሃን፤ ሚያዝያ 1/2018 (ኢዜአ)፦የትንሳኤ በዓልን በማስመልከት የግብርናና የኢንዱስትሪ ምርቶች በበቂ ሁኔታ መቅረባቸውን የደብረ ብርሃን ከተማ ነዋሪዎች ገለጹ።
የሰሜን ሸዋ ዞን ንግድና ገበያ ልማት መምሪያ በበኩሉ አምራቾች፣ አቅራቢዎችና የሕብረት ሥራ ማህበራትን በማስተባበር በተሰራው ሥራ ምርቶች በበቂ ሁኔታ ለማቅረብ መቻሉን አስታውቋል።
አስተያየታቸውን ለኢዜአ ከሰጡ ነዋሪዎች መካከል የደብረ ብርሃን ከተማ ነዋሪ አቶ ጌታቸው በላይነህ እንደገለጹት፤ ለትንሳኤ በዓል የእርድ እንስሳትና ሌሎች የግብርና ምርቶች በብዛትና በአይነት በገበያው ቀርበዋል።
ይህም ሸማቹ በአቅሙ ልክ የሚፈልገውን ገዝቶ በዓሉን በተረጋጋና በደስታ ለማሳላፍ እንደሚያስችላቸው ተናግረዋል።
ወይዘሮ ሰርካለም ገበያው በበኩላቸው በዛሬው እለት መካከለኛ ዶሮ 1ሺህ 400 ብር ከፍተኛው 1ሺህ 800 ብር እየተሸጠ መሆኑን ገልጸው በዓሉ እየቀረበ ሲመጣ ገበያው መረጋጋት እየታየበት መሆኑን ተናግረዋል።
የሻምበል፣ ነዋይና ጓደኞቻቸው የዶሮ እርባታ ህብረት ሽርክና ማህበር አባል ወጣት ሻምበል መንግስቱ እንዳለው ለትንሳኤ በዓል ከ11 ሺህ በላይ እንቁላል ለገበያ ማቅረባቸውንና አንዱን በ16 ብር እየሸጡ መሆናቸውን ተናግሯል።
የሰሜን ሸዋ ዞን ንግድና ገበያ ልማት መምሪያ ሀላፊ አቶ ዘውገ ንጉሴ እንደገለጹት፤ ለትንሳኤ በዓል አምራቹና ሸማቹ በቀጥታ የሚገናኙበት ምቹ ሁኔታ ተፈጥሯል ብለዋል።
በዚህም የእርድ እንስሳት፣ ዶሮና እንቁላልን ጨምሮ ሌሎች የግብርናና የኢንዱስትሪ ምርቶች የግብይት ሰንሰለቱ ባጠረ መንገድ ለሸማቹ ማህበረሰብ በተመጣጣኝ ዋጋ መቅረባቸውን አስረድተዋል።
ከተለያየ አካላት ጋር ትስስር በመፍጠር 81ሺህ ሊትር ዘይት፣ 12ሺህ ኩንታል ጤፍ፣ 2ሺህ ኩንታል ስኳር እንዲሁም ሽንኩርትና ሌሎች ለበዓሉ አስፈላጊ ምርቶች መቅረባቸውንም አመልክተዋል።
በከተማው አዲስ በተገነባ የገበያ ማዕከል የግብርናና የኢንዱስትሪ ምርቶች በተመጣጣኝ ዋጋ እየተሸጡ መሆኑንም አስረድተዋል።