በጋምቤላ ለትንሳኤ በዓል የሚያስፈልጉ ምርቶችና የእርድ እንስሳት በበቂ ሁኔታ ቀርበዋል - ኢዜአ አማርኛ
በጋምቤላ ለትንሳኤ በዓል የሚያስፈልጉ ምርቶችና የእርድ እንስሳት በበቂ ሁኔታ ቀርበዋል
ጋምቤላ ፤ ሚያዝያ 1/2018 (ኢዜአ)፦ በጋምቤላ ክልል ለትንሳኤ በዓል በምርቶችና እርድ እንስሳት በቂ አቅርቦት መኖሩን የክልሉ ንግድና ኢንዱስትሪ ቢሮ ገለፀ።
የትንሳኤ በዓልን በማስመልከት ያልተገባ የዋጋ ጭማሪ በሚያደርጉ ነጋዴዎች ላይ እርምጃ እየተወሰደ መሆኑንም ቢሮው አስታውቋል።
የቢሮ ኃላፊው አቶ ኮንግ ኡላንግ ለኢዜአ እንደገለፁት፤ ለትንሳኤ በዓል በሚያስፈልጉ ምርቶችና የእርድ እንስሳት እጥረት እንዳይከሰት አስፈላጊው ዝግጅት ሲደረግ ቆይቷል።
በዚህም ለበዓሉ የሚያስፈልጉ ምርቶችና የእርድ እንስሳት በበቂ ሁኔታ መቅረባቸውን ገልፀዋል።
የበዓል ገበያውም የተሳለጠና የህዝቡን የመሸመት አቅም ያገናዘበ እንዲሆን ቢሮው ግብረ ሃይል አቋቁሞ ቁጥጥርና ክትትል እያደረገ መሆኑን ተናግረዋል።
በዚህም ከአከፋፋይና ከቸርቻሪ ነጋዴዎች ጋር በመወያየትና ጥናት በማድረግ የኢንዱስትሪና የግብርና ምርቶች በተመጣጣኝ ዋጋ ለሸማቹ እንዲቀርብ እየተደረገ መሆኑን አመልክተዋል፡
ምክንያታዊ ያልሆነ የዋጋ ጭማሪ በሚያደርጉ ነጋዴዎች ላይ እርምጃ እየተወሰደ እንደሚገኝ የቢሮ ኃላፊው አስታውቀዋል።
የበዓል ግብይት ሲያከናውኑ ከነበሩ መካከል ወይዘሮ በለጠች አጂና በሰጡት አስተያየት ለበአል የሚያስፈልጉ ምርቶች በበቂ ሁኔታ መቅረባቸውን ተናግረዋል።
የዘንድሮው የበዓል ገበያ ከአምናው ተመሳሳይ ወቅት ጋር ሲነፃፀር በፍጆታ ምርቶች ላይ የዋጋ ጭማሪ መታየቱን ጠቅሰዋል።
በተለይም በዘይት፣ በሽንኩርት፣ በቲማቲም እና በሌሎችም ምርቶች እንዲሁም በእርድ እንስሳት ላይ የዋጋ ጭማሪ መታየቱን ለአብነት አንስተዋል።
በዘንድሮው የትንሳኤ በዓል የእርድ እንስሳት የተሻለ አቅርቦት መኖሩን የገለፁት ደግሞ በእርድ እንስሳት ንግድ ስራ ላይ የተሰማሩት አቶ ዘመኑ አረጋ ናቸው።
በምርቶች ላይ መጠነኛ የዋጋ ጭማሪ መታየቱንም ገልጸዋል።